አዲስ አበባ የቱሪስቶች መዳረሻ መዲና ሆናለች

You are currently viewing አዲስ አበባ የቱሪስቶች መዳረሻ መዲና ሆናለች

AMN – ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ በነበሯት ውስን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ምክንያት ለበርካታ አመታት ለቱሪስቶች ማቆያ ሳትሆን መተላለፊያ ከተማ እንደነበረች የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ ገለጹ፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ከኤ ኤም ኤን 24/7 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ከጥቂት አመታት ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በመዲናዋ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ማልማት ተችሏል ብለዋል፡፡

ለአብነትም በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለሸገር እና በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እውን መሆናቸው፣ በመዲናዋ ውስጥ እንደ የአንድነት ፓርክ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የእንጦጦ ፓርክ እና የሳይንስ ሙዚየም የመሳሰሉ ትላልቅ የቱሪስት መዳረሻዎችን መስራት መቻሉን ገልፀዋል ፡፡

በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማትና በወንዞች ዳርቻ ልማት በተሰሩ ስራዎች፣ መዲናዋ የቱሪስት መስህብነቷ እና ተመራጭነቷ በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የመስህብ መዳረሻዎች መስፋፋት፣ አዲስ አበባ ከተማ ለቱሪስቶች መተላለፊያ ሳትሆን፣ ቱሪስቶች ጊዚያቸውን የሚያራዝሙባት ከተማ እንድትሆን አስችሏታል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡ ይህም በመዲናዋ በቱሪዝም ዘርፉ የመጣ ትልቅ ለውጥ እንደሆነም ጠቁመዋል ፡፡

በመሆኑም መዲናዋን በ2018 በጀት አመት በ1ኛው ሩብ አመት ብቻ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ376 ሺ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እንደጎበኟትም ምክትል ኮሚሸነሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከ61.6 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉንና ይህም ለኢኮኖሚው ትልቅ ዓቅም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ለሆቴሎችና በስራቸው ለሚገኙ ሰራተኞች ከፍተኛ የስራ እድል ፈጥሯል፤ የውጭ ምንዛሬ እንዲጨምር አድርጓል፤ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ፍሰት በአዲስ አበባ እንዲያድግ አስችሏል፣ የቱሪስት ቁጥር ጨምሯል፣ መዲናዋም ከዚህ ተጠቃሚ ሆናለች ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ ተናግረዋል ፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review