የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ የተሰወረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

You are currently viewing የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ የተሰወረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

AMN ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ/ም

የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ የተሰወረን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው ህዳር 04 እና 05 ቀን 2018 ዓ/ም በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 06 ልዩ ቦታው 23 ቀበሌ መዝናናኛ ክበብ አካባቢ ነው፡፡

ተከሳሽ እሱ ያውቃል ቢያዝን ከባለቤቱ ከወ/ሮ ሐመልማል አለምነህ ጋር በትዳር ተጣምረው መኖር ከጀመሩ አራት ወራትን አስቆጥረዋል፡፡

ተከሳሽ ከባለቤቱ ጋር በኪራይ ከሚኖሩበት ቤት ህዳር 04 ቀን 2018 ዓ/ም ከጠዋቱ 4፡00 ሠዓት ሲሆን ከሌላ ወንድ ጋር ስልክ ትደዋወያለሽ በሚል ቂም በቀል በመነሳሳት ሟችን አንገቷን በማነቅ ህይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ በር ዘግቶባት ከአካባቢው ለጊዜው ይሰወራል፡፡

ተከሳሹ በዚሁ ብቻ አላባቃም ከአንድ ቀን በኋላ ህዳር 05 ቀን 2018 ዓ/ም ባለቤቱን ከገደለበት መኖሪያ ግቢ ተመልሶ በመምጣት ከእዚህ ቀደም ከባለቤቱ ጋር በሚፈጠረው ፀብ ያሸማግል የነበረን አለባቸው አየለ የተባለን ጎረቤቱን በሟች ባለቤቱ ይጠረጥረው ነበርና መሳሪያ በመተኮስ በስምንት ጥይት ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ከአካባቢው ሊሰወርም ችሏል፡፡

የወንጀሉ መፈፀም መረጃ የደረሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ምርመራና ክትትል ክፍሉ የወንጀል ስፍራው ላይ በመገኘት የሟች አለባቸው አየለን አስከሬን በማንሳትና ከአካባቢው በሰበሰበው መረጃ መነሻነት የሟች መኖሪያ ቤት ሲከፈት የሐመልማል አለምነህ አስከሬን ሊገኝም ችሏል፡፡

ፖሊስ ከወንጀሉ መፈፀም በመነሳት ተገቢውን የሰውና የኤሌክትሮኒክስ መረጃዎችን በመከታተል ተጠርጣሪውን ህዳር 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ሞላሌ ከተማ ከተደበቀበት መኖሪያ ቤት የግድያ ወንጀሉን ከፈፀመበት መሳሪያ ጋር በቁጥጥር ስር ሊያውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review