የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መከበር የቱሪዝም ፀጋዎች እንዲተዋወቁ ዕድል እንደሚሰጥ ተገልጿል
ከአዲስ አበባ በ2 መቶ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ወይን አደጋ የአየር ንብረት አላት፡፡ የመሬት አቀማመጧ ሜዳማና ተዳፋታማ ነው፡፡ ይህች ከተማ ሆሳዕና ናት፡፡ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በድምቀት ለማክበርና እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ ሸር ጉድ በማለት ላይ ትገኛለች፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ይህን መነሻ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር የቱሪስት መስህቦችን በአግባቡ እንዲተዋወቁ በማድረግ ረገድ ያለው አበርክቶ ምን እንደሚመስል ለመቃኘት ወድዷል፡፡
እየተደረገ ያለው ዝግጅት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የኮሙኒኬሽንና የሚድያ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብድልባር ኡስማን በጉዳዩ ዙሪያ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ የለውጡ ትሩፋት በሆነው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ያሉ የቱሪዝም ፀጋዎች በርካታ ናቸው፡፡ እንደነዚህ ያሉ በዓላት መከበራቸው ለክልሉ የበለጠ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ሴክተር መሆኑን ተከትሎ ለክልላችን ከሚያስገኘው ገቢ ባሻገር በጥቅል ሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ አሻራ ያኖራል ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ አቶ አብድልባር ገለፃ፤ በተፈጥሮ ሃብቶቿ የማትታማው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወንዞቿ፣ በተራሮቿ፣ በፏፏቴዎቿ እንዲሁም ሰው ሰራሽ መስህቦቿ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ከጀመረች ቆይታለች፡፡ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለማክበር የሚታደሙ እንግዶችን ለማስተናገድ በጉጉት እየጠበቀች እንደሆነም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሃሳባቸውን ያጋሩን ከፍተኛ የቱሪዝም ተመራማሪ እና መምህር አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሆሳዕና ከተማ እንዲካሄድ መደረጉ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ፀጋዎች ጎልተው እንዲወጡ ብሎም እንዲታወቁ በር ይከፍታል ብለዋል፡፡
እንደ አያሌው (ዶ/ር) ገለጻ፣ በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶች በተቻለ መጠን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊኖርባቸው አይገባም፡፡ በተለይ አስጎብኚዎች የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ክልሉ ላይ የሚገኙ ፀጋዎችን አንድ ሁለት ብለው ማስጎብኘት ይጠበቅባቸዋል። ሆቴሎችም ቢሆኑ ጥራት ያለው አገልግሎት ከሙሉ መስተንግዶ ጋር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አቶ አብድልባርም በበኩላቸው፤ 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ለማክበር ቁጥራቸው እስከ 50 ሺህ የሚጠጉ እንግዶች ከውጭ እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለሁሉም እንግዶች በቂ ማረፊያዎች ስለመዘጋጀቱ እንዲሁም በቂ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባሶች ከሆቴሎች ወደ ፕሮግራሙ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች እንግዶችን ለማመላለስ ተዘጋጅተዋል፡፡ ከተሞቻችን የብልፅግና ተምሳሌት እንዲሆኑ የልማት ስራዎችን በተፋጠነ መንገድ በመስራት የአመራር ትኩረትና ክትትልን ከአዲስ የስራ ባህል ጋር አወዳጅቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደሆነው የሚናገሩት ኃላፊው፣ ክልላቸው 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የማክበር እድል እንዳገኘ ከታወቀበት ሰዓት ጀምሮ ተገቢው ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የመሰረተ ልማት ስራዎችን የማስፋፋት በተለይም ከተሞችን በማስዋብ ፅዱ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የገጠር ኮሪደርንም በክልሉ በአራት ዞኖች (ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ሀላባና ከምባታ ዞኖች) አስጀምረው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ተደርጓል፡፡ ኢንሼቲቩን በማስፋፋት የክልሉ መንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠውን አደራ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያሉ ፀጋዎች
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስር የሚገኙ ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ የክልሉ ሰላም የተጠበቀ እንዲሁም እንግዶችን ቀና በሆነ ስነ ምግባር ለማስተናገድ የተዘጋጀ ማህበረሰብ ስለመኖሩ የሚናገሩት አቶ አብድልባር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ7 ዞኖች፣ በ3 ልዩ ወረዳዎች፣ በ50 ወረዳዎች እና በ29 የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ አደረጃጀት ነው፡፡ ሆሳዕና የአስተዳደርና ፖለቲካ መቀመጫ መሆኗን አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ፀጋዎች ብሔራዊ ፓርክና ጥብቅ ደኖች፤ ተራራዎች፣ ሸለቆዎች፣ ፏፏቴዎች፣ ሃይቆች፣ ፍል ውሃዎች እና ትክል ድንጋዮች መሆናቸው ተለይቷል። አቶ አብድልባር በአስተያየታቸው፣ “የሚዳሰሱ ብሎም የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆናችን መጠን የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ብሎም ደግመው እንዲመጡ አስቻይ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡ የሚጎበኙ ፀጋዎችን በተመለከተ በጉራጌ ዞን የጀፎረ-የጉራጌ ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ፣ ጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ፤ ቆጠር ገድራ ጥብቅ ደን)፤ በሀዲያ ዞን (ቦዮና ቡደ መዳ ሀይቆች፤ ኦሊዳ ዋሻ፤ አገሜና ሆጄ ፏፏቴ)፣ በምስራቅ ጉራጌ ዞን (የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ፣ ጥንታዊ ምድረ ከብድ አቦ ገዳም)፤ በስልጤ ዞን (ሀረ ሼጣንና አባያ ቱፋ ሀይቆች)፣ በከምባታ ዞን (የሀምባርቾ 777 ተራራ፣ የሶድቾ ዋሻ)፣ በሀላባ ዞን (አርቶ ፍል ውሃና ፋማ ፏፏቴ)፣ የም ዞን (“ሳሞ ኤታ” ዓመታዊው የየም የባህላዊ መድኃኒት ለቀማ ስነ ስርዓት፣ ጥንታዊ አንጋሪ ቤተ መንግስት)፤ በቀቤና ልዩ ወረዳ (ጥንታዊና ታሪካዊ ዘብሞላና ቃጥባሬ መስጅዶች)፤ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ (የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ)፤ በማረቆ ልዩ ወረዳ (የፈቃ ከንፈልቻ ጥንታዊ ዋሻ) እንዲሁም የክልሉ ብሔረሰቦች የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ የተለያዩ ዓመታዊ በዓላት ያሏቸው ሲሆን መስቀል በጉራጌ፣ ያሆዴ በሀዲያ፣ መሳላ በከምባታ፣ መንገሳ በሀላባ፤ ሄቦ በየም፣ መሳላ (መሪሾ) በጠምባሮ እና ሌሎች ያልተጠቀሱ የክልሉ ጸጋዎች ናቸው” ብለዋል፡፡

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አከባበር በርካታ መርሃ ግብሮች የሚከናወኑበት ሆኖ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብዝሃ ከተሞች አንዷ በሆነችው ወልቂጤ ከተማ በዓሉ በባዘር እና ኢግ ዚቢሽን ይከበራል። ዋናውና ማጠቃለያ ሁነት ሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡ ከህዳር 25 እስከ 29 የወንድማማቾች ቀን፣ የአብሮነት ቀን፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቀን፣ የምክክር ቀን እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ቀን በሚል በድምቀት እየተከበሩ ይገኛል። መርሃ ግብሮችን በተመለከተ የተለያዩ ሲምፖዚየሞች ተዘጋጅተዋል፡፡ የፎቶ አውደ ርዕይ፣ ፓናል ውይይት በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶች የሚጎበኝበት አግባብ ጭምር ስለመዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
እንደ አያሌው (ዶ/ር) ገለፃ፤ በዓሉ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መከበር መቻሉ ቱባውን ባህል ምንም ሳይበረዝ ለማየት እድል ይፈጥራል፡፡ የክልሉ ማህበረሰብ የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአኗኗር ዘይቤ ምን ይመስላል? የሚለውን በቅርበት የማየቱን እድል ሰፊ ያደርገዋል። በክልል ከተሞች የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ለመጎብኘት እድሉን ያገኘ እንግዳ ቀጣይ ሌሎችን ሰዎች ጭምር ይዞ ለመምጣት ፍላጎት ያድርበታል፡፡ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ክልሎች በርካታ ጎብኚዎች እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን ከገቢ አንፃርም ከፍተኛ አበርክቶ አለው፡፡
የበዓሉ መከበርን ፋይዳ አያሌው (ዶ/ር) ሲገልጹ፣ የቱሪዝም ፀጋዎች እንዲተዋወቁ ያደርጋል። ኢንቨስትመንትን ያበረታታል። ኢኮኖሚውን ያነቃቃል፤ የሥራ ባህል ያሻሽላል፡፡ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ እንደሀገር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ ባህላቸውን፤ ማንነታቸውን በማስተዋወቅ ማህበራዊ መስተጋብር ያጠናክራል፡፡ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጠናከር፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ገዥ ትርክት እንዲሠርፅ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
በሄለን ጥላሁን