ኢትዮጵያ የሕጻናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት እጥረት በመቀነስ ውጤታማ ሥራ እየሰራች ነው

AMN- ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የሕጻናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነት እጥረት በመቀነስ ውጤታማ ሥራ እየሰራች መሆኗን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ በ11 የአፍሪካ ሀገራት የሕፃናት የምግብ እጥረትን ለመከላከል የተደረገውን የሦስት ዓመት ፕሮግራም ግምገማና የልምድ ልውውጥ እያካሄደ ነው።

በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የሦስት ዓመት ፕሮግራም ግምገማና የልምድ ልውውጥ መድረኩ ለአራት ቀናት ይቆያል፡፡

የጤና ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር መብራቱ ማሴቦ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ሀገራት የሕፃናትን የምግብ ደኅንነት የሚያረጋግጥ ትብብር በመገንባት በትኩረት መሥራት አለባቸው።

የአህጉሪቷን የሕፃናት የምግብ እጥረት ለማስተካከል የተደረገው የሦስት ዓመት ፕሮግራም የአፍሪካ ሀገራትን ጥረት በመደገፍ አዎንታዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህ በኩል በኢትዮጵያ የሕፃናትን አጣዳፊ የምግብ እጥረትን (መቀጨጭን) ለመቀነስ ውጤታማ ስራ ከሚሰራባቸው የአህጉሪቷ ሀገራት መካከል አንዷመሆኗን ጠቁመዋል።

በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን የበለጠ በማሳደግ የሕፃናትን ሁለንተናዊ የምግብ ደኅንነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የሚሲዮን ኃላፊ፣ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካ ካሶሎ በበኩላቸው፤ የልጆች አመጋገብ የትውልድ ግንባታን የሚወስን ወሳኝ ኢንቨስትመንት ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ሕፃናትን የምግብና ሥነ-ምግብ ደኅንነትን ለማረጋገጥም ሀገራት የውስጥና የልማት አጋሮችን አቅም በመጠቀም ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መድረኩ የሕፃናትን የዕድገት ሁኔታ የሚወስን የጋራ መግባባት፣ ልምድና ተሞክሮን በመቀመር ትብብርን ለማጠናከር እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review