የጥንታዊ ዕቃዎች አዲስ መድረክ – በአዲስ አበባ

You are currently viewing የጥንታዊ ዕቃዎች አዲስ መድረክ – በአዲስ አበባ

‎AMN- ታህሳስ 2/2018 ዓ.ም

‎ዘመናዊ የቤት ውስጥ መገልገያዎችና ሌሎች ጥንታዊ ቁሶች የሚገኙበት ልዩ ስፍራ በመዲናችን ብቅ ብሏል። ይህ ቦታ ያለፈውን ዘመን ታሪክ በህያውነት ለሚናፍቁ ሰዎች መድረክ ሆኗል።

‎የዚህ ስብስብ ባለቤት የሆኑት አቶ ተፈራ ተስፋዬ፣ ዕድሜ ጠገብ የሆኑ ዕቃዎችን በመሰብሰብና በመሸጥ ይታወቃሉ። ‎ከመቶ ዓመታት በፊት በነበሩበት ገጽታ ሳይለወጡ፣ የዘመኑን ውበትና ጥንካሬ ይዘው የቆዩ ቁሶችን መሰባሰብ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል።

‎የጥንታዊ የቤት ቁሳቁሶችን የመሰብሰብ ፍቅር ያደረባቸው ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሆነ ይገልጻሉ። አቶ ተፈራ ዕቃዎቹን መሰብሰብ የጀመሩት ከአሥር ዓመታት በፊት ሲሆን፣ የሰበሰቧቸውን ቁሳቁሶች ደግሞ ለደንበኞች መሸጥ የጀመሩት ከስድስት ዓመታት ወዲህ ነው።

‎አቶ ተፈራ የድሮ ዕቃዎች ለእርሳቸው ትልቅ ስሜት እንደሚሰጧቸው እና እንደሚያወሯቸው በመግለጽ፣ ነፍስ እንዳላቸው አድርገው ይገልጿቸዋል። እነዚህ ጥንታዊ ዕቃዎች የቀድሞውን ዘመናዊነት የሚያሳዩ ሲሆን፣ እንደ ዕቃው ዓይነት ዋጋቸው እንደሚለያይም ተናግረዋል።

‎ከተሰበሰቡት እና ከሚሸጡት ዕቃዎች መካከል፣ የሸክላ ማጫወቻዎች፣ የፎቶ ፍሬሞች፣ ቴሌቪዥኖች፣ ካሴቶች፣ የሙዚቃ ማጫወቻዎች፣ ካሜራዎች እና ሌሎችም የቤት ውስጥ መገልገያዎች ይገኙበታል። እነኚህ የድሮ ዕቃዎች ጥንካሬ እንዳላቸው የሚገልፁት አቶ ተፈራ፣ የእቃዎቹ ጥንካሬ ዘመኑን እንደሚናገር እና የዚያን ዘመን ሰዎች ምን ያህል ጥንቁቆች እንደነበሩም ያስረዳሉ።

‎አንዳንድ ጊዜ የገዟቸውን ዕቃዎች ሲያጸዱ የእቃዎቹን ጥንካሬ በገዛ ዓይናቸው እንደሚመለከቱ ጠቁመው፣ አሠራሩ ከአሁኑ ዘመን ጋር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለውም ይናገራሉ። አቶ ተፈራ የሰበሰቧቸው አንዳንድ ጥንታዊ ዕቃዎች ዋጋቸው በውጭ ሀገሮች እስከ 9 ሺህ ዶላር እንደሚሸጡ ተናግረዋል።

‎ነገር ግን እሳቸው የሚሸጡት ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡት የሙዚቃ ማጫወቻ ቴፖች ሲሆኑ፣ እስከ 30 ሺህ ብር እንደሚሸጡ ገልጸዋል። አቶ ተፈራ ቦሌ ሚሊኒየም አከባቢ በሚገኘው ሱቃቸው ያሰቧሰቧቸውን ጥንታዊ የቤት መገልገያ ቁሶች፣ የድሮውን ለማስታወስ ብቅ የሚሉ መኖራቸውን ይጠቁማሉ።

‎አያይዘውም፣ እነዚህን ጥንታዊ ዕቃዎች ለመግዛት የሚጓጉ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ እንደነዚህ ያሉ ታሪካዊና ጠንካራ ዕቃዎችን መሰብሰብ መልካም ልማድ እንደሆነ ለወጣቶች ምክራቸውን ለግሰዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review