ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለከተማችን ነዋሪዎች አዲስ ድንቅ ሌላ ስጦታ የሆነውን “የእንጦጦ – ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት” እንዲሁም የቀበና ግድብ ፕሮጀክትን መርቀዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለከተማችን ነዋሪዎች አዲስ ድንቅ ሌላ ስጦታ የሆነውን “የእንጦጦ – ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት” እንዲሁም የቀበና ግድብ ፕሮጀክትን መርቀዋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሰኔ 21/2018

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ለከተማችን ነዋሪዎች አዲስ ድንቅ ሌላ ስጦታ የሆነውን “የእንጦጦ – ቀበና የወንዝና የወንዝ ዳርቻ ልማት” እንዲሁም የቀበና ግድብ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መርቀዉልን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ አበባችን የነዋሪዎቿን ጥያቄዎችና መሰረታዊ ፍላጎቶች በተጨባጭ እየመለሰች፤ ለህዝባችን ቅድሚያ የሚሰጣቸውንና ከተማዋ የሚመጥናትን ታላላቅ የልማት ስራዎች ሁሉ በላቀ ብቃትና ትጋት እያከናወነች ትገኛለች።

ዛሬ ለከተማችን አዲስ አበባ ድምቀትና ተጨማሪ ጌጥ እና የውበት ፀዳል ያላበሰውን ይህን የወንዝ ዳርቻ እና የግድብ ልማት በክቡር ጠቅላይ ሚስትራችን ሀሳብ አመንጪነት በተሰጠን የስራ መመሪያ መሰረት በጥራትና በፍጥነት አጠናቀን ለህዝብ አቅርበናል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ ከተሰሩት ሌሎች የኮሪዶር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ጋር ተዋህዶ ሲታይ በእርግጥም አዲስ አበባ በአለም አቀፍ ደረጃ ምርጧ የቱሪስት መዳረሻ ብቻ ሳትሆን የውበት ማማ የሚያደርጋት ድንቅ ፕሮጀክት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 87.6 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ 10.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው።

በውስጡም እጅግ ማራኪ የሆኑ የጋራ አገልግሎት መስጫዎችንና የህዝብ መገልገያዎችን አሟልቶ ይገኛል።

ይህም 1 ትልቅ ግድብ፣ 16 አነስተኛ ግድቦች፣ 3 ቼክ ዳሞች፣ 1.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሃይኪንግ፣እንዲሁም 20.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ድጋፍ ግድግዳን (Retaining Wall) ያካተተ ነው።

የተፈጥሮ ውበቱን ይበልጥ ለማጉላትም 3 ማራኪ ፏፏቴዎች እና 1 የውሃ ምንጭ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን፣ የመሬት ጥበቃን ለማረጋገጥ 36,928 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የኮንሶ ጋቢዮንና የኮንሶ እርከን ስራዎች ተሰርተውለታል ብለዋል።

ልማቱ ለተፈጥሮ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ 59.7 ሄክታር የሚሸፍን ውብ የአረንጓዴ ልማት ስፍራን ያበለፀገ ሲሆን፣ 50,330 የተለያየ ዝርያ ያላቸው ዛፎችም ተተክለውበታል።

ከመሰረተ ልማት አቅርቦት አኳያ 10.62 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የአስፋልት መንገድ፣ 33.2 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች፣ እና 33.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን ዘመናዊ የመንገድ መብራት ዝርጋታ ተከናውኗል ብለዋል።

በተጨማሪም 19.13 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ እና የጎርፍ ማስወገጃ መስመር፣ እንዲሁም 23 ንፁህ የመጸዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል።

ጎብኚዎች ወንዙን በቀላሉና በውበት እንዲሻገሩ ለማስቻል 21 የእግረኛ ድልድዮች፣ 3 ተንጠልጣይ ድልድዮች፣ 6 የእግረኛ የብረት ድልድዮች፣ 1 ሰርኩላር ድልድይ እና 1 የኮንክሪት ድልድይ ተሰርተዋል።

ማህበረሰቡ ዘና እንዲልና የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኝ በማሰብ፤ 9 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ በአንድ ጊዜ 695 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ 7 የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች)፣ 4 የመሰብሰቢያ ስፍራዎች፣ 7 ፕላዛዎች እና 4 ፓቪሊዮኖች ተገንብተዋል።

ለንግድና ለመዝናኛ አገልግሎት የሚውሉ 32 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሱቆች፣ 2 አንፊ ቲያትሮች፣ 10 ካፍቴሪያዎች፣ 7 የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ እንዲሁም 2 አነስተኛ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ተካተውበታል።

በመጨረሻም፣ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በታለመለት የጊዜ እና የጥራት ደረጃ እንዲጠናቀቅ ሌሊት ከቀን የደከማችሁና የታተራችሁ ያስተባበራችሁና የደገፋችሁ በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች፣ እንዲሁም ለመላው የአካባቢው ማህበረሰብ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review