ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለፁ።
በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው 17ኛው የአፍሪካ የመከላከያ መሪዎች ጉባዔ ተጠናቋል።
ጉባኤው አህጉሪቱ እየተጋፈጠች ያለችውን የሽብርተኝነት፣ መፈንቅለ መንግሥት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎች የደኅንነት ቀውሶችን በተባበረ ክንድ መፍታት ላይ ያለመ ነው።
መሪዎቹ የአፍሪካን የሠላምና የፀጥታ ችግሮችን የሌላ አህጉር ጣልቃ ገብነት ሳይስፈልግ እንዴት በራስ አቅም ብቻ መፍታት እንደሚቻል በዝርዝር ተወያይተዋል።
ለቀናት በልዩ ልዩ አፍሪካዊ ጉዳዮች ሲመክር የቆዬው የመከላከያ መሪዎች ጉባኤ ቀጠናዊ ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ በሶማሊያ አልሸባብን የመዋጋት ተግባራት፣ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ፣ በየሀገራቱ ያለው የውስጥ ግጭት፣ ለሠላም ማስከበር ተልዕኮ የፋይናንስ ድጋፍ በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ኢትዮጵያ ለሠላም ካላት ጠንካራ አቋምና እንደ አፍሪካዊ ተምሣሌትነቷ ተመርጣ ይህንን ጉባኤ ለተከታታይ ዓመታት እያስተናገደች መሆኗን ያነሱት የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን ለመፍታት ኢትዮጵያ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።
ጉባኤው እያንዳንዱ የአፍሪካ ቀጠና ተግዳሮቶች ያሉበት በመሆኑ ችግሮችን በፍጥነት የሚፈታ የተባበረ የአፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል አስፈላጊነት ላይ መወያየቱን የገለፁት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ከራሷም አልፎ ለአህጉሪቱ ያላት አስተዋፅኦ የተንፀባረቀበትና ገፅታችንን ከፍ ያደረገ ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከጠቅላላው ጉባኤው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ከሀገራት ጋር መደረጉንም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ ሕዝብ ሠላም ላበረከተው አስተዋፅኦ በስብሰባው ከፍተኛ እውቅና መሰጠቱን ያወሱት በመከላከያ የዓለም አቀፍና የጎረቤት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ በቀጣይም የአህጉሪቱን ችግሮች በትብብር እየፈቱ ለመሄድ ከስምምነት መደረሱን ገልፀዋል።
የሁሉም የአፍሪካ አባል ሀገራት የሚሳተፉበት ይህ የአፍሪካ የመከላከያ መሪዎች የሠላምና ደኅንነት ጉባኤ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ለተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ ተመርጣ ስታስተናግድ መቆየቷን ከሃገር መከላከያ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡