የባቡር ኮርፖሬሽን ትርፋማነት ከ3.4 ቢሊየን ወደ 43 ቢሊየን ብር አድጓል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የባቡር ኮርፖሬሽን ትርፋማነት ከ3.4 ቢሊየን ወደ 43 ቢሊየን ብር አድጓል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ኅዳር 17/2019 ዓ.ም

ከጥቂት ዓመታት በፊት የውጭ አስተዳደር ይደረግበት የነበረውና በገቢው የሰራተኛ ደሞዝ እንኳን ለመክፈል ይቸገር የነበረው የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን፣ በተወሰደው የሪፎርም እርምጃ አስደናቂ ለውጥ በማስመዝገብ ዓመታዊ ትርፉን 43 ቢሊየን ብር ማድረስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ኢኮኖሚን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ ቀደም ሲል ኮርፖሬሽኑ ያስመዘግበው የነበረው ትርፍ 3.4 ቢሊየን ብር ገደማ ብቻ እንደነበር አውስተዋል።

የሪፎርሙ ውጤት በአገልግሎት አሰጣጥና በመሰረተ ልማት አቅም ግንባታም በግልጽ መታየቱን አንስተዋል፡፡

የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ ሎኮሞቲቮች ቁጥር ከ11 ገደማ ከነበረበት ወደ 36 ማደጉንም ተናግረዋል።

ጋሪዎችም ከ560 ወደ ከ1 ሺህ በላይ ከፍ ያሉ ሲሆን፣ የባቡሩ የጉዞ ፍጥነትም በሰዓት ከ37 ኪሎሜትር ወደ 55 ኪሎሜትር መሻሻሉን ገልጸዋል።

ዓመታዊ የመንገደኛ አገልግሎት ከ198 ሺህ ወደ 588 ሺህ ከፍ ማለቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የካርጎ ጭነትም ከ1.3 ሚሊየን ቶን ወደ 4.3 ሚሊየን ቶን ማደጉን ተናግረዋል።

ቢያንስ 95 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የቡና የወጪ ንግድ እና 25 በመቶ ገደማ የሚሆነው ማዳበሪያ ከውጭ የማስገባት ሥራ በባቡር እየተከናወነ ይገኛል።

ሰበታ አካባቢ የሚገኘውን የባቡር መጫኛና ማውረጃ ፖርትን ጨምሮ ከ15 ኪሎሜትር በላይ የባቡር መስመር በሀገር ውስጥ አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ በመሬት መንቀጥቀጥና በድልድይ መፍረስ የደረሰውን ጉዳት ጨምሮ እና ከኮምቦልቻ እስከ ሐራ ገበያ ያሉ ቀሪ የባቡር ሥራዎች በውስጥ አቅም እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እስከ አሁን ወደ 100 ኪሎሜትር የሚጠጋ ሥራ ተጠናቆ ቀሪው ከአንድ አመት እስከ አንድ አመት ተኩል ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጠቁመዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review