AMN – ኅዳር 17/2019 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሪፎርምና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት ጉድለት ለማስተካከል የለውጥ ሥራዎቹ ፍኖተ ካርታንና ሥርዓተ ትምህርትን በመቀየር መጀመራቸውን ገልጸው፣ ከዚህ ጎን ለጎን ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ስምንት ዓመታት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት እንዲሁም በሕዝብ ተሳትፎ 35 ሺህ የሚጠጉ የሕፃናት መዋያዎች መገንባታቸውን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ይህም ሕፃናት ወደ መደበኛ ትምህርት ሲገቡ መሠረታዊ ዕውቀት ይዘው እንዲገቡ የሚያስችልና ውጤቱም ቀስ በቀስ የሚታይ የመሠረት ሥራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት ሚኒስቴር 50 የሚጠጉ የሞዴል እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት 40 ገደማ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በሁሉም ክልሎች እየተስፋፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
የፌዴራል መንግሥት በሥርዓተ ትምህርትና በትምህርት ቤት ግንባታ ብቻ ሳይወሰን በመጻሕፍት ሕትመት፣ በዲጂታል ላይብረሪ ማስፋፋት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በመምህራን አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተለይም በዘንድሮው ዓመት የዲጂታል ፈተና ሥርዓቱን ይበልጥ ለማሻሻል እየተሠራ በመሆኑ የትምህርት ሥርዓቱ ከ90 በመቶ በላይ እንደሚስተካከልና በቀጣዮቹ አራትና አምስት ዓመታትም የሚፈለገውን የጥራት ደረጃ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተጓዳኝም የመምህራን ሥልጠና በስፋት እየተሰጠ መሆኑን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራት ማረጋገጫ ሥራዎች መጠናከራቸውን እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ግንባታም በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
እነዚህ የፍኖተ ካርታ፣ የመጻሕፍት፣ የዲጂታል ላይብረሪና የመምህራን አቅም ግንባታ ሥራዎች ተደምረው የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ የተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩት አብራርተዋል።
በአስማረ መኮንን