ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ እንብርት የሚገኘውን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎብኝተናል ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ከዓድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ታሪክ አለው፡፡ በዚህም የተነሣ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ጊዜ እንደ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በእሳት እስከ መቃጠልና ጥቁር ቀለም እስከ መቀባትም ደርሷል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ደረጃውን በጠበቀና ልዩ ልዩ ባለሞያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየታደሰ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡

የዓድዋ ሙዝየም በአካባቢው መገንባቱ፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ዐደባባይ ጥገና መደረጉ እና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከል እየሆነም ነው፡፡
አሁን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያን ሕንጻና ግቢ ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ ደግሞ፣ ታሪኩን የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የሕንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የጥበበ ዕድ እና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ አስደናቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የቤተ ክርስቲያኑ እና የአካባቢው ጥገና አሁን ከጀመርናቸው የከተማ ማዘመን ሥራዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡