ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲፈጸም በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ዝግጅት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የተጻፈ “የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ተመርቋል።

በመጽሐፍ ምረቃ ወቅት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት የሃይማኖት አባቶች አባገዳዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ በመንግሥት በፀጥታ ተቋማት ላይ ውጤታማ ሪፎርም መካሄዱን ገልጸዋል።
ይህ ሪፎርም የፀጥታ ተቋማት በነጻነት፣ በሰብዓዊ መንገድ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ባለፈው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲፈጸም የፀጥታ ተቋማት የላቀ ሚና መጫወታቸውን አስታውሰዋል።

በቀጣይ የሚካሄደው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን አቀፍ ሆኖ እንዲከናወን ዝግጅት መጀመሩንም ገልጸዋል።
”የምርጫ ደህንነትና የፀጥታ ተቋማት ሚና” የተሰኘው መጽሐፍ ፖሊሳዊ ሪፎርም በተካሄደበት ወቅት መመረቁ ሪፎርሙን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
መጽሐፉ በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ለፀጥታ አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል