የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታማኝ ግብር ከፋዮች የቅድሚያ መጠቀሚያ ካርድ ሰጠ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታማኝ ግብር ከፋዮች የቅድሚያ መጠቀሚያ ካርድ ሰጠ

‎AMN ታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም

‎የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የገቢ አሰባሰብ አቅም ለማሳደግና ከግብር ከፋዩ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የውይይት መድረክ አካሄደ።

‎በመድረኩ ላይ ለታማኝ ግብር ከፋዮች የአገልግሎት ቅድሚያ የሚያሰጣቸውን የልዩ መጠቀሚያ ካርድ (Privilege Card) የመስጠት መርሀ-ግብር ተከናውኗል።

‎በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን እንደገለጹት፤ የከተማዋ የገቢ አሰባሰብ እድገት እያሳየ ቢሆንም፣ ከከተማዋ አጠቃላይ የምርትና አገልግሎት ስሌት (GDP) አንጻር ሲታይ ግን አሁንም ጉድለቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

‎ከተማዋን ለመለወጥ የገቢ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሀላፊው፣ ለዚህም አስተዳደሩ ተቋማዊ ሪፎርሞችን እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

‎በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው በስራቸው ላይ የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተዋል።

‎በገቢዎች ቢሮ የሚደረጉ የገበያ ጥናቶች ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀው፣የዴስክ ኦዲት (Desk Audit) አሰራር አመታዊ ክፍያ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና ለማሳያነት ጠቅሰ

‎ ከዚህ በተጨማሪ በተቋሙና በግብር ከፋዩ መካከል ያለው መተማመን ሊጎለብት እንደሚገባ የሚሉ ሀሳቦች በስፋት ተነስተዋል።

‎ለተነሱት ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የገቢዎች ቢሮ ሀላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ፣ የገበያ ጥናት የሚደረገው ግብር ከፋዩ ላይ ጫና ለመፍጠር ሳይሆን “አንደር ኢንቮይስን” (ከእውነተኛ ዋጋ በታች ደረሰኝ መቁረጥን) ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል።

‎ግዢና ሽያጭ በተከናወነበት ትክክለኛ ዋጋ ልክ ደረሰኝ እንዲቆረጥ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።

‎አስተዳደሩ በሰው ሀይል ክህሎትና በአሰራር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ ለግብር ከፋዩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

‎አገልግሎት አሰጣጡን ተገልጋይ ተኮር ለማድረግ ጠንካራ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን፣ በቀጣይም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መሰል የውይይት መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ  ተገልጿል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review