ሴት ደራሲያን የዘመናት ታሪክን በመቅረፅ፣ ማህበራዊ ለውጥ በመምራት እና የዓለምን የሥነ ጽሑፍ ገጽታ በማበልጸግ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ብዕራቸውን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ ለረጅም ጊዜ የተድበሰበሱ ጉዳዮችን በግልጽ በማንሳት እና የሴቶችን፣ የህጻናትንና በዙሪያቸው ያለውን ተሞክሮ በማሳየት የዓለምን ግንዛቤ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፤ በማበርከት ላይም ይገኛሉ። ከእነዚህ ደራሲያን መካከል አንዷ ማክዳ አርሺ ነች፡፡
ማክዳ አርሺ ማን ነች?
ሙሉ ስሟ ማክዳ ሁሴን አርሺ ነው። በአብዛኛው ሰው ዘንድ የምትታወቀው ግን ማክዳ አርሺ በሚለው ነው፡፡ ደራሲ ማክዳ በሙያዋ ነርስ ነች፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊት ስትሆን የምትኖረው በአሜሪካን ሀገር ነው፡፡ ማክዳ ታዋቂ የልጆች መጽሐፍት ደራሲ ነች። በሥነ ጽሑፍ ዓለም ትኩረቷን ያደረገችው በተለይም በሕፃናት እና ወጣቶች ላይ ሲሆን፤ ማንነትን መቀበል፣ በራስ መተማመን እና ማህበራዊ ተቀባይነት ላይ የሚያጠነጥኑ ስራዎችን በመጻፍ ትታወቃለች። የሶስት ሴት ልጆች እናት መሆኗ ደግሞ ለልጆች ሥነ ጽሑፍ ያላትን ፍቅርና ትኩረት የበለጠ እንዳጎላው ይነገራል።
የማክዳ አርሺ ሥራዎች ዋነኛ መገለጫቸው ለሕፃናት አእምሮ የሚመጥን ቀላል አቀራረብ በመጠቀም ጠንካራ ማኅበራዊ መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻላቸው ነው። ጸሐፊዋ በተለይ ሴት ልጆችና ኦትስቲክ (ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች) የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ጫናዎች በመጋፈጥ፣ የራሳቸውን ምርጫ ተከትለው ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ታበረታታለች። በኦቲዝም ላይ ባተኮረው መጽሐፏ ማኅበረሰቡ የአዕምሮ ዕድገት ልዩነት ያላቸውን ልጆች እንዴት መቀበልና መደገፍ እንዳለበት የበኩሏን አስተዋፅዖ አድርጋለች።
የማክዳ ስራዎች
“Shining As I Am” (“እንዳለሁ አበራለሁ”) የተሰኘው መጽሐፍ ከደራሲ ማክዳ አርሺ ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ መጽሐፍ ለጸሐፊዋ ትልቅ እውቅናን ያስገኘላት ሥራ ሲሆን፣ ኦቲዝም (Autism) ያለበት አንድ ልጅ ታሪክን የሚተርክ መጽሐፍ ነው።
የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ስለ ኦቲዝም ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን አንድ ኦቲስቲክ የሆነ ልጅ የቀኑን ውሎ በሚያሳይ መልኩ ከራሱ አንደበት የተተረከበት ነው፡፡ ታሪኩ ህፃናት ኦቲዝም ምን እንደሆነ፣ በቀላልና ግልፅ በሆነ ቋንቋ እንዲረዱ ከማስቻሉም በላይ በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበትና ጥንካሬ የሚያጎላም ጭምር ነው፡፡
ደራሲ ማክዳ አርሺ፣ ኦቲስቲክ ልጆች ዓለምን የሚገነዘቡበት መንገድ ልዩ መሆኑንና ይህም እንደ እርግማን ሳይሆን እንደ ተፈጥሯዊ የአእምሮ እድገት ልዩነት ሊታይ እንደሚገባ አስረድታበታለች፡፡
በእንግሊዝኛ “Shining As I Am” በሚል ርዕስ የወጣውና በአማዞን ላይ “Best Seller” ለመሆን የበቃው የደራሲዋ የህፃናት መጽሐፍ “እንዳለሁ አበራለሁ’’ በሚል በታገል ሰይፉ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል፡፡
የማክዳ ሌላኛው ስራዋ “The World Needs a Uniquely Happy You” ይሰኛል፡፡ ይህ መጽሐፍም “የዓለም መብራቶች” በሚል በጋዜጠኛ አንተነህ ከበደ አማካኝነት ተተርጉሟል፡፡ ይህ የልጆች መጽሐፍ ሁሉም ሰው የራሱን ባህል፣ ማንነት እና ልዩነት እንዲያከብር የሚያበረታታ ነው። ዓለም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ማንነት ልዩ እና ደስተኛ ሆኖ ሲገኝ ውበት እንደሚኖራት በማስገንዘብ ወጣት አንባቢዎች ራሳቸውን እንዲወዱና ልዩነታቸውን እንዲያከብሩ ያነሳሳል፡፡
ዓለም አቀፍ ሽልማቶች
ማክዳ ግሎው ቡክስ ገጸ-ድር ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው ደራሲዋ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች እና ህጻናት ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጫና ተገንዝባ ዝም ማለት አልፈቀደችም። ወጣት አንባቢዎችን በተለይም ሴት ልጆችን ለማበረታታት መጽሐፍ መፃፍ እንደሚያስፈልግ ከውሳኔ ላይ ደረሰች። ይህ ስራዋ ደግሞ ለበርካታ ሽልማቶች አብቅቷታል፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ደራሲ ማክዳ አርሺ በ10 ወራት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት ያገኘችው በቅርቡ ነው፡፡ ማክዳ፤ “Shining As I Am” (እንዳለሁ አበራለሁ) በተሰኘው የልጆች መጽሐፍ በ“International Impact Book Award” ዘርፍ የ2025 አሸናፊ ለመሆን ችላለች፡፡
በአሜሪካ አሪዞና ግዛት ፊኒክስ ከተማ በተካሄደ ታላቅ የሽልማት ሥነ ስርዓት ላይ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ መጽሐፍ ሽልማት ዘርፍ ይኸው “Shining As I Am” (እንዳለሁ አበራለሁ) መጽሐፍ አሸናፊ ሆኖ ደራሲዋ ሽልማቷን ተቀብላለች።
መጽሐፉ በሚያስተላልፈው ጠንካራ መልዕክት እና በልጆች ሥነ-ጽሑፍ ላይ ባበረከተው አስተዋጽኦ ለዚህ ክብር መብቃቱ ተገልጿል። ይህ ድል ለደራሲ ማክዳ አርሺ ትልቅ ስኬት ከመሆኑም ባሻገር፣ የመጽሐፉ መልዕክት በዓለም ዙሪያ ላሉ በርካታ አንባቢያን እንዲደርስ ያግዛል።
ደራሲዋ በዚሁ “Shining As I Am” (እንዳለሁ አበራለሁ) በተሰኘ መጽሐፍ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አራት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝታለች።
“International Impact Book Award” በዓለም ዙሪያ በአንባቢያን ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ፣ አዎንታዊ ለውጥን የሚያበረታቱ እና ጠቃሚ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ መጽሐፍትን እውቅና የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። አውስትራሊያ እና እንግሊዝን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡ ደራሲያንም ይሳተፉበታል። ሁነቱ ደራሲዋ ኢትዮጵያንና ራሷን ለዓለም ያስተዋወቀችበትን አጋጣሚም የፈጠረ ነበር፡፡
በተመሳሳይ “The World Needs A Uniquely Happy You” (“የዓለም መብራቶች”) የተሰኘው ስራዋም በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ‘የብሔራዊ የእናቶች የመጽሐፍ ምርጫ’ (Mom’s Choice Awards) አሸናፊ በመሆን እውቅና አግኝቷል።
ይህ ሸላሚ ድርጅት የማክዳ መጽሐፍ ለራስ እውነተኛ መሆን፣ ማንነትን መረዳት እና ልዩ ባህሪያትን የመቀበል አስፈላጊነት የሚያስተምር፣ ልብ የሚነካ እና በጎ አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ሽልማቱ ይገባታል ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በAuthors Reading በተዘጋጀው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የሥነ ጽሑፍ ውድድር ይህ መጽሐፍ አንድ ዘርፍ በሆነው “Children’s book concept” ዘርፍ የ Pencraft Books Award ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ማክዳ ሮያል የድራጎንፍላይ ቡክ አዋርድ፣ የኦተር ሾት፣ መንትዮቹ ባቡ እና ቡባ የንባብ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎችንም ሽልማቶች አግኝታለች፡፡
በአጠቃላይ የማክዳ አርሺ ሥራዎች ዋነኛ መገለጫቸው ለሕፃናት አእምሮ የሚመጥን ቀላል አቀራረብ በመጠቀም ጠንካራ ማህበራዊ መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻላቸው ነው። ማክዳ አርሺ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽልማት የታጀቡ የልጆች መጽሐፍትን በመጻፍ፣ በተለይም በማንነት፣ በልዩነት እና በራስ መተማመን ዙሪያ ጠቃሚ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ራሷንና ሀገሯን ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ ያለች ኢትዮጵያዊቷ ደራሲ ነች።
በጊዜው አማረ