“የምግብ ዋስትና ‘ሥራ የለኝም፣ ጥሪት መቋጠር አልችልም፣ የራሴንና የልጆቼን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ከበደኝ …’ የሚሉ ጭንቀት የወለዳቸውን ጥያቄዎች መልሶልኛል”
መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ወ/ሮ እየሩሳሌም መቻል
በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል ለተረጂነት ያጋልጣል፡፡ ተረጂነት ይዟቸው የሚመጣቸውን መዘዞችን መቀበል የውዴታ ግዴታ ይሆናል፡፡ ተረጂነት ከግለሰብ አልፎ የማህበረሰብ እና የሀገር መገለጫ ሲሆን ደግሞ ተፅዕኖው ሉዓላዊነትን እስከመገዳደር የሚደርስ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል ርዕስ ግንቦት 2016 ዓ.ም. በተዘጋጀ ሰነድ መግቢያ ላይ የሰፈረውን ሃሳብ መመልከት እንደሀገር ለዘመናት የኖርንበትን የተረጂነት አስተሳሰብ እና ውጤት መራር ሐቅ በመግለጥ ነገሩን ለመረዳት ያግዛል፡፡
በሰነዱ ላይ እንደሰፈረው፤ ኢትዮጵያ በየጊዜው የተቃጣባትን የውጭ ወረራና የገዥነት አስተሳሰብ ሕዝቦቿ በአንድነት ቆመው በመመከት ሉዓላዊነቷን አስከብረው ለትውልድ አስረክበዋል። ይህ የአልገዛም ባይነት አስተሳሰብና ተግባር ከሀገራችን አልፎ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ሆኗል፤ ነጻነታቸውንም እንዲያረጋግጡ አግዟል፡፡ ይሁን እንጂ እንቢ ለባርነት በማለት ለነጻነት የተፋለሙት ኢትዮጵያዊያን ለም መሬት ላይ ተቀምጠው፣ ድህነትን ለማስወገድ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የተላመዱት እስኪመስሉ ድረስ ለዘመናት አብረው ዘልቀዋል፡፡
“ድህነት፤ በየጊዜው የሚፈጠረውን ጦርነት እና እጅግ ኋላቀር የሆነውን አስተሳሰብ እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ተረጂነት ገዢ ቦታ እያገኘ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በሌላ ሰው መረዳት እና ልመና እንደ ነውር መቆጠሩ ቀርቶ እንደ መብትና ዋነኛ የመተዳደሪያ መንገድ የሚያይ የህብረተሰብ ክፍል እንዲበራከት ዕድል ፈጥሯል፡፡” የሚለው ሰነዱ፤ ለእርዳታ እጁን የሚዘረጋ ደግሞ እርዳታውን ተከትሎ ከረጂው የሚመጡ በርካታ መዘዞችን መቀበሉ ግድ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ስለዚህ የተረጂነትን እና የልመናን አስተሳሰብ ማስወገድ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በጋራ መትጋት እንደሚገባ አፅንኦት ይሰጣል፡፡
ከግለሰብ እስከ ሀገር ዋጋ የሚያስከፍለውን የተረጂነት አስተሳሰብ በማስወገድ ራስን በመቻል ጥረት ውስጥ ገብተው በምሳሌነት የሚነሱት በርካቶች ናቸው፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በሥራቸው ተረጂነትን ድል የነሱ በሺዎች ከሚቆጠሩ የመዲናችን ታታሪዎች መካከል የወይዘሮ እየሩሳሌም መቻል እና የወይዘሮ ወርቅነሽ ጫካን የሕይወት ተሞክሮ ለመዳሰስ ወደድን፡፡
እነዚህ በስም የጠቀስናቸው ግለሰቦች ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነታቸው ባለፈ የሚያመሳስላቸው በርካታ ጉዳይ አለ።
ለአብነት እነዚህ ሁለቱ (ወይዘሮ እየሩሳሌም እና ወይዘሮ ወርቅነሽ) ያለ አባት የሚያሳድጓቸው ልጆች አሏቸው፡፡ ልጆቻቸውን ለማሳደግ እና ለማስተማር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሥራ በማጣት ወይም የሚያገኙት ገቢ ዝቅተኛ በመሆኑ የኑሮ ፈተና አማርሯቸዋል፡፡ ከዚህ ፈተና ለመውጣትም አማራጮችን ለመጠቀም የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም በከተማ ደረጃ ተግባራዊ በሆነው የምግብ ዋስትና (ሴፍትኔት) መርሃ ግብር በመታቀፍ ያስመረራቸውን ድህነት ተበቅለውታል፡፡ ነጋቸውን ከዛሬ የተሻለ ለማድረግም ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ለመሆኑ በምን ዓይነት መንገድ ተጉዘው ከተረጂነት ወጡ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በአንደበታቸው ካካፈሉን ሃሳብ እየጨለፍን እንመልከት፡፡
ወይዘሮ እየሩሳሌም መቻል፤ ነዋሪነታቸው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተለምዶ ቀጠና ስድስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በአካባቢያቸው ራሳቸውን ለመለወጥ እና ኑሯቸውን ለማሸነፍ ከሚጥሩ ትጉህ ሠዎች አንዷ ስለመሆናቸው የየዕለት እንቅስቃሴያቸው ምስክር ነው፡፡ “በጣም ችግረኛ እና በሰዎች ላይ ጥገኛ ነበርኩ፡፡ ያለአባት የማሳድጋቸውን አራት ወንድ ልጆች መንከባከብ በጣም ከብዶኝ ቆይቻለሁ፡፡ ለዕለት ጉርስ ፍለጋ በተመላላሽ የቤት ሠራተኛነት አገልግያለሁ፡፡ ልብስ አጥቤያለሁ፣ እንጀራ ጋግሬያለሁ፡፡ የቀን ሥራ ሠርቻለሁ፡፡ ግን ከችግሬ መውጣት ሳልችል ቆይቻለሁ” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ በትላንት እና በዛሬው የሕይወት ምዕራፋቸው ለውጥ ውስጥ የምግብ ዋስትና (ሴፍትኔት) መርሃ ግብር በድልድይነት ስለማገልገሉ ያስረዳሉ፡፡
እንደሳቸው ገለፃ፤ የምግብ ዋስትና ‘ሥራ የለኝም፣ ጥሪት መቋጠር አልችልም፣ የራሴንና የልጆቼን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ከበደኝ …’ የሚሉ ጭንቀት የወለዳቸውን ጥያቄዎች መልሶላቸዋል። በቤት ውስጥ ከመቀመጥ አውጥቶ ከሥራ ጋር አገናኝቷቸዋል። ከሠዎች ጋር አስተዋውቋቸዋል። ከጥገኝነትም አላቋቸዋል፡፡ የተሻለ ገቢ በማግኘት የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ፍላጎት በተሻለ ሁኔታ ማሟላት ችለዋል። ከገቢያቸው ላይ ወደ መቆጠብ ተሸጋግረዋል፡፡ የተለያዩ ስልጠናዎችንም በመውሰድ አስተሳሰባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን አሻሽለዋል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ በማለፍ ዛሬ ላይ የደረሱበትን ደረጃም፤ “በተሰጠኝ የድጋፍ እና ባጠራቀምኩት የቁጠባ ገንዘብ የራሴን የሻይ ቡና ሥራ ጀምሬያለሁ። በሂደትም ፈጣን ምግቦችን ወደ ማዘጋጀት አሳድጌያለሁ፡፡ አሁን ላይ ሥራዬን በማሻሻል ምግብ እያዘጋጀሁ በመሸጥ ላይ እገኛለሁ፡፡ ለአንድ ሠራተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ፡፡ ለዚህ ውጤት የወረዳው አስተዳደር የ15 ሺህ ብር ገንዘብ እና የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጎልኛል፡፡ በቀጣይ ከራሴ እና ከልጆቼ አልፌ ለሌሎች የምተርፍ ውጤታማ ሠራተኛ ለመሆን አቅዳለሁ፡፡ ይህንንም አሳካለሁ” በማለት አብራርተዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የሆኑት ወይዘሮ ወርቅነሽ ጫካ ደግሞ፤ በልብስ ስፌት ሥራ ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ ወይዘሮዋ እንዳስረዱት፤ ሴፍትኔት በአንድ እጅ ከማጨብጨብ የሚያላቅቅ ነው፡፡ ሥራ ለመሥራት ፍላጎትና ሙያ ኖሯቸው፤ ያንን ለማድረግ የገንዘብ ወይም የሃሳብ እጥረት ችግር ለሆነባቸው ሰዎች ጥሩ መፍትሄ መስጠት የቻለ ነው፡፡
ይህንንም ራሳቸውን በምሳሌነት በመጥቀስ፤ “እኔ የልብስ ስፌት ሙያ እያለኝ፣ ለሥራው የሚሆን ማሽን መግዢያ ገንዘብ ስለሌለኝ በኑሮዬ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሳላመጣ ቆይቻለሁ። በሴፍትኔት መርሃ ግብር በመታቀፌ ለማሽን መግዢያ የሚሆን ገንዘብ በድጋፍ እና በቁጠባ አግኝቻለሁ። አሁን ላይ ሁለት ማሽኖች አሉኝ፡፡ ከሴፍትኔት ባገኘሁት ገንዘብ አንድ ማሽን ገዝቼ ወደሥራ ገብቻለሁ፡፡ የእኔን ትጋትና ለውጤን ያዩ አቅም ያላቸው ሰዎች ድጋፍ አድርገውልኝ ሌላ ተጨማሪ ማሽን አስገብቻለሁ” ብለዋል፡፡
የአንድ ሴት እና የአንድ ወንድ ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ወርቅነሽ፤ ብቻቸውን ያሳደጓቸው ልጆች ራሳቸውን ወደሚችሉበት ደረጃ እያደረሱ ይገኛሉ። የዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ሴት ልጃቸው እና የ9ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ወንድ ልጃቸውን የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ የልብስ ስፌት ሙያንም በማሰልጠን ከትምህርት ቤት መልስ ያላቸውን ጊዜ በሥራ ላይ እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆነዋቸዋል፡፡
በመዲናችን አዲስ አበባ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድህነት መውጫ እርካብ ሆኗቸዋል፤ እየሆናቸውም ይገኛል፡፡ የተረጂዎችን ለእርዳታ የተዘረጋ እጅ ወደ ልማት እንዲዞር አድርጓል፡፡ ያለንን ፀጋ ለማየት የጋረደንን የአስተሳሰብ ደመና በመግለጥ፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የማይተካ ሚና ስለተጫወተው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት የኑሮ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ኢዶሳ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ መርሃ ግብሩ መተግበር የጀመረው በ2009 ዓ.ም. ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩ ባሉ 119 ወረዳዎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡ በዓለም ባንክ ድጋፍ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ተከናውኗል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተፈጻሚ በሆነው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር 349 ሺህ 207 እንዲሁም በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 107 ሺህ 407 የሚሆኑ ዜጎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 456 ሺህ 605 የሚሆኑት ቆይታቸውን በአግባቡ በማጠናቀቅ ተመርቀዋል፡፡ በተጨማሪም፤ ከካናዳ መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ ባለ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር 19 ሺህ 20 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በያዝነው የ2018 በጀት ዓመት ታኅሣስ 30 ላይ ይመረቃሉ፡፡
የኑሮ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ አክለው እንዳብራሩት፤ በአጠቃላይ ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በመዲናዋ እየተተገበረ ባለው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር 609 ሺህ 487 ዜጎች ተጠቅመዋል። በጾታ ከተመለከትን 392 ሺህ 78 ሴቶች፣ 217 ሺህ 409 ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡
የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች በዕድሜያቸው ከ18 እስከ 60 ዓመት የሆናቸው ሲሆን፤ በጽዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በቀላል የተፋሰስ ልማት፣ በአነስተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ላይ በቀን ለአራት ሰዓታት ይሳተፋሉ። በዚህም በቀን 203 ብር ገቢ ያገኛሉ፡፡ በአንድ ቤተሰብ መስፈርቱን ያሟሉ አራት አባላት በመርሃ ግብሩ የመታቀፍ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
“የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር መተግበሩ ለተጠቃሚዎችም ሆነ ለከተማዋ ከፍተኛ ጠቀሜታ አበርክቷል” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይህንንም እንደሚከተለው አብራርተዋል፤ በተጠቃሚዎች ረገድ ካየነው፤ ከከፋ የድህነት ኑሮ በመውጣት ራሳቸውን በዘላቂነት እንዲችሉ አድርጓል፡፡ የሠው እጅን ከመጠበቅ ወይም ከጥገኝነት ተላቅቀዋል፡፡ የሕይወት ክህሎት፣ የገንዘብ አያያዝና አጠቃቀም፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎችን የሚወስዱበትን ዕድል አግኝተዋል። በዚህም የአስተሳሰብ፣ የዕውቀትና የሙያ መሻሻልን አምጥተዋል። የሥራ ባህላቸውን አዳብረዋል። ማህበራዊ መስተጋብራቸውን አጠናክረዋል፡፡ ከሚያገኙት ገቢ 20 ከመቶ ቆጥበዋል። የሚቆየውን መርሃ ግብር ሲያጠናቅቁ፤ 600 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ይሰጣቸዋል። በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ፣ የቆጠቡትን ገንዘብ እና ያገኙትን የ600 ዶላር ድጋፍ በማቀናጀት በመረጡት የሥራ መስክ ላይ ይሰማራሉ፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በኑሯቸው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችለዋል፡፡ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ዜጎች ሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉም ብዙ ናቸው፡፡
ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ የተመቸ አካባቢ የመፍጠር ሥራ ውጤታማ እንዲሆን፣ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ፣ የሥራ አጥነት ምጣኔ እንዲቀንስ፣ አምራች የሠው ኃይል እንዲጨምር በማድረግ የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር ለከተማዋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ለመዲናዋ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ በመርሃ ግብሩ በተገኘ ድጋፍ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች 128 የምገባ ማዕከላት፣ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ከ400 በላይ መጸዳጃ እና ሻውር ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልፀዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 14፣ በኮልፌ 4 በድምሩ 19 ሼዶችን በመገንባት በዶሮ እርባታ እና በከብት ማድለብ ሥራ ላይ ለተሰማሩ አንቀሳቃሾች መሰጠቱንም አስታውሰዋል፡፡ 4 ባለ አራት ወለል ሕንጻዎችን (በአዲስ ከተማ፣ በቂርቆስ፣ በየካ እና አቃቂ ቃሊቲ) በመገንባትና ለተደራጁ 292 ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ አስገብቷል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በወቅቱ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “የከተማ አስተዳደራችን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት በመለወጥና ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችሉ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል” ሲሉ ለጉዳዩ ስለተሰጠው ትኩረት አብራርተዋል።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በመንግስትና በዓለም ባንክ እንዲሁም በካናዳ መንግስት ድጋፍ ሲተገበር በቆየው እና እየተተገበረ ባለው የምግብ ዋስታና መርሃ ግብር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከአስከፊ ድህነት ወጥተው በሥራ ራሳቸውን መለወጥ ችለዋል፡፡ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ምንጭ ለመሆን የበቁም ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ጅምር ያለንን ፀጋ በመጠቀም ከግል እስከ አገር ለመለወጥ ያለንን ዕድልና አቅም ያሳያል፡፡ ስለሆነም ለውርደትና ለጫና የሚዳርገውን የተረጅነት አስተሳሰብ በተግባር በተደገፈ የሥራ በትር በመቅጣት ድህነትን ማስወገድ ይገባል፡፡ ወደ ተሟላ የዕድገትና ብልፅግና ጉዞ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ያኔ ነፃነትና ሉዓላዊነቱ የተጠበቀ፣ ከጫናና ከተፅዕኖ የተላቀቀ፣ አንገቱን ቀና ያደረገ ሕዝብና አገር የመሆን ህልማችን ይሳካል።
በደረጀ ታደሰ