አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች ላይ የወሰደችው እርምጃ የቡድኑን አፍራሽ አካሄድ ለዓለም ያጋለጠ ነው

You are currently viewing አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች ላይ የወሰደችው እርምጃ የቡድኑን አፍራሽ አካሄድ ለዓለም ያጋለጠ ነው

AMN ሰኔ 11/2018

አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ የቡድኑ አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የጣለችው የቪዛ እገዳ፣ የቡድኑን ጽንፈኝነትና አፍራሽ አካሄድ ለዓለም ማኅበረሰብ ያጋለጠ ነው ሲሉ የስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጠዓመ ዓረዶም ገለጹ።

አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን መግለጿ ይታወቃል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ የቪዛ እገዳ የተጣለው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ተሳታፊ ናቸው በተባሉ አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ ነው፡፡

የስምረት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጠዓመ ዓረዶም ውሳኔውን አስመልክተው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ እርምጃው የአሜሪካ መንግስት የቀድሞው ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን በትግራይ ክልል ውስጥ እያደረገ ያለውን የጦርነት ትንኮሳና የሰላም ስምምነቱን የማፍረስ ሴራ በተገቢው መንገድ የተረዳ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

አሜሪካ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በቅርበት ስትከታተል እንደነበረችም ውሳኔው ማረጋገጫ ነው ሲሉ አክለዋል።

ጽንፈኛው ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ጊዜው ያለፈበትንና የፈረሰውን ምክር ቤት በድጋሚ በማዋቀር የራሱን ፕሬዝዳንትና አዲስ ካቢኔ መምረጡ ለግጭትና ሁከት መዘጋጀቱን ያሳያል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ ቡድኑ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅትና የጦርነት ትንኮሳዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ስለሆነም አሜሪካ በዚህ ወቅት የወሰደችው እርምጃ ለሰላም ፈላጊዎች ትልቅ የምስራች መሆኑን ጠቁመው፤በትግራይ ህዝብ ላይ የሰላም እጦትና ጦርነት የሚደግሰውን ቡድን ለይቶ የመታ ነው ብለዋል።

አሁን የተወሰደው እርምጃ የሁሉም የትግራይ ሰላምና የለውጥ ፈላጊ ኃይሎችና የፓርቲያቸው ትግል ያመጣው ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፣ሆኖም ግን እርምጃው ከዚህ በላይ ሊጠነክር እንደሚገባ አመልክተዋል።

ቡድኑ እስካሁን እያደረገ ያለው ተግባር ግልጽ የአሸባሪነት ስራ ነው ያሉት አቶ ጠዓመ፤ ልክ እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ሁሉ ይህ ቡድንም በአሜሪካ መንግስትና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ በልዩ ሁኔታ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባል ብለዋል፡፡

የቡድኑን አጥፊ እንቅስቃሴ የዓለም ማኅበረሰብ በሚገባ እንዲገነዘበው ፓርቲያቸው ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የፌዴራል መንግስትም ሕገ-መንግስታዊ ኃላፊነቱን በመጠቀም የቀድሞው ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር ስራውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review