ኢትዮጵያ በሚገኘዉ ባንግላዴሽ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ሸረፉል እስላም በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማቱ ሲጀመር በስራዉ ፍጥነትና ጥራት በጣም ተደንቄ ነበር ይላሉ፡፡
ያንጊዜ ወደ ኤርፖርት የሚወስደዉ መንገድ፤ አዳዲስ የእግረኞች እና የብስክሌት መንገዶች እየተገነቡ ነበር፤በጣም የሚገርመዉ ደግሞ ይሔ ሁሉ ስራ በስድስት ወራት ዉስጥ መጠናቀቁ ነው ፡፡
ሌሎች በመዲናዋ የተገነቡ የኮሪደር ልማት ስራዎችም በተመሳሳይ መልኩ በፍጥነት እና በጥራት ተገንብተዉ ተጠናቀዋል።

የተሰሩት የኮሪደር ልማት ስራዎች በጣም ንጹህ ናቸዉ፤ፓርኮች፤ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች፤ የሌሊት መብራት፤የሚያማምሩ የዘንባባ ዛፎች እና አካፋይ መንገዶች አሏቸው፡፡
ወታደራዊ አታሼዉ ብርጋዴር ጀነራል ሸረፉል እስላም በተሰራዉ የኮሪደር ልማት ከመደሰታቸዉ የተነሳ “አሁን ኤርፖርት ሄጄ እንግዳ ስቀበል በኩራት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሬ ደስተኛ ነኝ ሲሉ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ መዲና ናት፤ የህዝብ ብዛቱ እና የትራፊክ ፍሰቱ ሁሉንም ማስተናገድ ይችላል፤ አዲስ አበባን መጥታችሁ ጎብኙ፤ ስለ መዲናዋ ያላችሁ እሳቤ ሙሉ በሙሉ ይቀየራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የተገነቡት መሰረተ ልማቶች አስቀድመው የታቀዱ መሆናቸውን የሚናገሩት ወታደራዊ አታሼዉ አዲስ አበባ በ10 እና 20 አመታት ውስጥ ልዩ ገጽታ ልትላበስ እንደምትችልም ገልጸዋል፡፡
አሁን ለብዙ ሰዎች አዲስ አበባ ውስጥ እንደምኖር ስናገር ኩራት ይሰማኛል፤ እንዲያውም ባለቤቴ አንዳንድ ጊዜ ከአዲስ አበባ አልሄድም፣ እዚሁ እቀራለሁ ትላለች ሲሉ በአዲስ አበባ ከተማ ልማት መማረካቸውን ተናግረዋል፡፡
ከባንግላዴሽ እኛን ለመጠየቅ የሚመጡ ዘመዶቻችን አዲስ አበባን ወደዋት ነው የሚመለሱት፤ በጣም ጥሩ የአየር ሁኔታ፣ በጣም ጥሩ ሰዎች፣ እና በአሁኑ ጊዜ በጣም ጥሩ መሰረተ ልማት አለ። የሌሊት ዕይታውም ደግሞ በጣም አስደናቂ ነው ሲሉ አግራሞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ