AMN – ነሐሴ 10/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማን የመጠጥ ውሃ የማምረት አቅም በቀን ወደ 910 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማድረስ ችለናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላፉት አራት በጀት ዓመታት ሲሰራባቸው የቆያቸውንበቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ የመጠጥ ውሃ ማምረት የሚችለውን ፕሮጀክት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ ማጣራት የሚችለውን የኮዬ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክትን መርቆ ለአገልግሎት አብቅቷል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከተማዋ ከለውጡ በፊት በቀን 525 ሺህ ሜትር ኪዩብ ይመረት የነበረውን የመጠጥ ውሃ በቱሉ ጉዶ፣ በለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት፣ በበረከት የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳ እና ሌሎች አካባቢዎችንም በማልማት የከርሰ ምድር ውሃን በስፋት በመጠቀም በአሁኑ ወቅት በቀን ከ910 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የተመረቀው በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ የሚያመርተው ፕሮጀክት የነዋሪዎችን ጫና በእጅጉ እንደሚቀንስም አመላክተዋል፡፡
ከተማ ማለት ህንጻ ብቻ ሳይሆን ንጹህ አየር፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ጤናማ አካባቢ እና ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ያለው ለመኖር ምቹ አካባቢ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ በተያዝው በጀት ዓመትም በቀን ተጨማሪ 130 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማምረት የሚያስችል ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አብስረዋል።
በታምራት ቢሻው