ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ድል ለመመለስ ኒውካስትል ዩናይትድን ያስተናግዳል

You are currently viewing ማንችስተር ዩናይትድ ወደ ድል ለመመለስ ኒውካስትል ዩናይትድን ያስተናግዳል

AMN ታኅሣሥ 17 ቀን 2018 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ ሲጀምር ማንችስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ ኒውካስትል ዩናይትድን ያስተናግዳል።

ዛሬ እኤአ ዲሴምበር 26 በብሪታንያ “ቦክሲንግ ደይ” ይከበራል። ከገና በዓላቸው በኋላ ትልቅ ቦታ ያለው ስጦታ የሚበረከትበት ዕለት ነው።

በዚህ ዕለት በበዓል ስሜት ውስጥ ያሉ ደጋፊዎችን የበለጠ ለማዝናናት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አወዳዳሪ አካል በርካታ ጨዋታዎችን በማድረግ ይታወቃል።

ዘንድሮ ግን የማንችስተር ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ጨዋታ ብቻ ይከናወናል።

ምሽት 5 ሰዓት የሚደረገው ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ ነው።

በሳምንቱ መጨረሻ በአስቶንቪላ የተረታው ዩናይትድ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል።

ሩበን አሞሪም የቡርኖ ፈርናንዴዝ እና ኮቢ ማይኑ መጎዳት የአማካይ ክፍሉን አሳስቶበታል።

በአስቶንቪላው ጨዋታ በቅጣት ያልተሰለፈው ካሲሜሮ ወደ ሜዳ መመለሱ ግን ለአሰልጣኙ ትልቅ እፎይታ ይሰጣል።

ትልቁ ጥያቄ ብራዚላዊውን አማካይ ከማን ጋር ያጣምራል? የሚለው ነው።

ማኑኤል ኡጋርቴ ጥሩ ብቃት ላይ አለመሆኑ አሰልጣኙን አማራጭ አሳጥቷል።

ሩበን አሞሪም በቪላው ጨዋታ ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እንዲሁም ወጣቱን ጃክ ፍሌቸርን በተወሰነው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠቅሟል።

በዛሬው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ተከላካዮቹ ሀሪ ማጓየር እና ማቲያስ ደሊግት በጨዋታው አይሳተፉም።

ኒውካስትል ዩናይትድ ወጥ ብቃት ለማሳየት ተቸግሯል። ከመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ አሸንፏል።

በሳምንቱ መጨረሻ ከቼልሲ ጋር ባደረገው ጨዋታ 2ለ0 ሲመራ ቆይቶ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ይታወሳል።

ኒውካስትል ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ያለው የቅርብ ጊዜ ክብረ ወሰን የሚያኩራራ ነው።

በሁሉም ውድድር ባደረጋቸው አምስት የመጨረሻ ጨዋታ አራቱን አሸንፏል።

ባለፈው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ በኦልድትራፎርድ 2ለ0 ፣ በሜዳው ሴንት ጀምስ ፓርክ ደግሞ 4ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል።

በዛሬውም ጨዋታ ይህን የበላይነቱን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል።

ትልቁ ችግር “በቦክሲንግ ደይ” ያለው ታሪክ ደካማ መሆኑ ነው።

ኒውካስትል ዩናይትድ “በቦክሲንግ ደይ” ባደረጋቸው ጨዋታዎች 16 ጊዜ ተሸንፏል። ይህም በሊጉ መጥፎ ታሪክ ሆኖ ተመዝግቧል።

ማንችስተር ዩናይትድ በአንፃሩ በ”ቦክሲንግ ደይ” 22 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በሊጉ ማንም ያላደረገው ታሪክ አፅፏል።

ከእነዚህ ድሎች ውስጥ ሦስቱን ያገኘው የዛሬ ተጋጣሚው ኒውካስትል ዩናይትድን በመርታት ነው።

ሁለቱ ክለቦች ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ በ”ቦክሲንግ ዴይ” ይጫወታሉ።

ጨዋታው ምሽት 5 ሰዓት በዋና ዳኛ አንቶኒ ቴይለር ፊሽካ ይጀመራል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review