የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አቅም በማሳደግ ሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂ፣ የአዲስ አበባን ስማርት ሲቲ ግንባታ እውን ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሸንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እንደታወቀው፣ ስትራቴጂውና የከተማዋ ስማርት ሲቲ ግንባታ ተቀናጅተው እየተተገበሩ ይገኛሉ።
የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስታንዳርድ ዝግጅትና ሬጉላቶሪ ቡድን መሪ አቶ ዮናስ ደምሰው ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደተናገሩት፣ ዕቅዱ በዋናነት የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ተደራሽ ማድረግ፣ የዜጎችን የዲጂታል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እና በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት በዘመናዊ ሥርዓት ማጠናከር ላይ ያተኩራል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በኮሪደር ልማት ውስጥ የተገጠሙ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ሲሆኑ፣ እነዚህም የኢንተርኔት፣ የሲሲቲቪ ካሜራ እና የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የያዙ ናቸው።

በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድም የ”መሶብ” አንድ ማዕከል አገልግሎት እና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መዘርጋታቸው የከተማዋን ስማርት ሲቲ ጉዞ እያፋጠኑት ይገኛሉ።
ከዚህ ባለፈም እንደ “ኢትዮ-ኮደርስ” ያሉ ሥልጠናዎች ዜጎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው በሀገር ውስጥ ሆነው ለውጭ ድርጅቶች በመሥራት የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ቡድን መሪው ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ ስኬቶችን በተመለከተም፣ በአሁኑ ወቅት በጤናው ዘርፍ የሳንባ ኤክስሬይ ምርመራን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) መሥራት መጀመሩ ተገልጿል። በተመሳሳይ በትምህርት ዘርፍ ውድ የሆኑ የላቦራቶሪ ቁሳቁሶችን በኤ አይ ሴሙሌሽን በመተካት ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አቶ ዮናስ አስረድተዋል።
የዜጎችን የመረጃ ደኅንነትና የዳታ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥም፣ የከተማዋን የዳታ ፍላጎት የሚያሟላ ዘመናዊ የዳታ ማዕከል ለመገንባት ጥናት ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁ ተረጋግጧል።
ይህ ማዕከል ከተማዋ በየቀኑ የምታመነጨውን መረጃ በአግባቡ በመሰብሰብ ለጤና፣ ለትምህርትና ለከተማ ልማት አገልግሎቶች ለማዋል ያስችላል ተብሏል።
በአጠቃላይ እየተከናወኑ ያሉ የዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታዎች የአዲስ አበባን ስማርት ሲቲ ራዕይ ከማሳካት ባለፈ፣ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እየጫወቱ መሆኑን አቶ ዮናስ ገልጸዋል።
በሔለን ተስፋዬ