AMN – ግንቦት 10 ቀን/ 2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን በ13ኛው ዓለም-ዓቀፍ የከተሞች ፎረም ላይ በባኩ፣ አዘርባጃን እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገለጹ፡፡

ፎረሙ፣ “ቤት ለሁሉም፤ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ጠንካራ ከተሞች እና ማህበረሰቦች” በሚል መሪ ሐሳብ እየካሄደ ሲሆን፤ ዓለም አቀፋዊ የመኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት፣ ዘላቂ የከተማ ልማት፣ ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ከተሞች፣ የአየር ንብረት እና የመኖሪያ ቤት ግንኙነቶች፣ መልሶ ግንባታ እና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ይመከርባቸዋል፤ ልምድ ልውውጥ እና የመስክ ጉብኝትም ይካሄዳል ብለዋል ከንቲባ አዳነች።

ከንቲባ አዳነች አክለውም ቡድኑ ከውይይቶች እና ከመስክ ጉብኝቶች በተጨማሪ፣ የሀገራችን ኢትዮጵያን ብሎም የመዲናችንን አዲስ አበባ ገፅታ ለዓለም ማስተዋወቅ የሚችል እና በዛሬው ዕለት በተከፈተው ኤክስፖ መንግስት ከግል ዘርፍ ጋር በመተባበር ሀገራችን ኢትዮጵያን የሚገልፅ ፓቪልዮን (ቡዝ) በመውሰድ በተለያዩ መንገዶች የተዘጋጁ መረጃዎች በፅሁፍ፣ ቪድዮ እና Virtual Reality (VR) ወዘተ. በመጠቀም ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡