አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ጥረት ምን ለውጥ እያመጣ ነው?

You are currently viewing አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ጥረት ምን ለውጥ እያመጣ ነው?

በአዲስአበባ 347 አገልግሎቶ ችበቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሰጡ ይገኛሉ

“ከዚህ ቀደም የይዞታ ማረጋገጫ ለማውጣት ብዙ ጊዜ ተመላልሻለሁ፡፡ ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ በብዙ ልፋት ነው ካርታውን ያወጣሁት፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጥ በመሆኑ ቀልጣፋ ሆኗል፡፡ በሲስተም አማካኝነት ስልኬ ላይ በሚደርሰኝ መልእክት መሰረት ወደሚመለከተው ክፍል በመሄድ አገልግሎት አግኝቻለሁ፡፡ ጊዜዬንም በአግባቡ መጠቀም ችያለሁ፡፡” ይላሉ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ የሆኑትና ካርታቸውን ወደ ኢ-ካርታ (ኤሌክትሮኒክስ ካርታ) ለማስቀየር መጥተው ያገኘናቸው አቶ ፍትህአወቅ አሰፋ፡፡

አቶ ፍትህአወቅ በአገልግሎቱ ደስተኛ እንደሆኑና በተለይ ሰራተኞች በቅንነት ተቀብለው በትዕግስት እንዳስተናገዷቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ሲስተሙ ላይ የሚታየውን መጓተት መቅረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ሌላኛው ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አገልግሎት ሊያገኙ መጥተው ያነጋገርናቸው አቶ ተመስገን ሰፊው ይባላሉ፡፡ እሳቸውም የኢ-ካርታ አገልግሎት ለማግኘት ነበር የተገኙት።

“ከዚህ ቀደም በመሬት ዘርፍ ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት አድካሚና ወረፋ የሚበዛበት ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰጥ በመሆኑ ጥሩና ቀልጣፋ የሚባል መስተንግዶ በአጭር ጊዜ አግኝቻለሁ፤ ጊዜና ወጪዬን ቆጥቦልኛል፤ አሁን በቶሎ ወደ ታክሲ ስራዬ እመለሳለሁ” ብለዋል፡፡ አቶ ተመስገን እንደገለፁት፣ አገልግሎቱ በሲስተም የታገዘ በመሆኑ የተገልጋዩንም ምልልስ መቀነስ አስችሏል፡፡ በስልክ በሚደርሳቸው መልእክት መሰረት ጉዳያቸውን ተከታትለው ክፍያ ሲከፍሉ ቆይተው የኢ-ካርታ (ኤሌክትሮኒክስ ካርታ) አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

አቶ ይድነቃቸው በንቲ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ነዋሪ ናቸው፡፡ ቤት ገዝተው በስማቸው እንዲመዘገብላቸው የስም ዝውውር አገልግሎት ለማግኘት ተገኝተው ነበር ያገኘናቸው፡፡ አገልጋዮች ባላቸው አቅም በቅንነት አገልግሎት ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉ ቢሆንም ሲስተሙ ላይ ችግር እንዳለ ያነሳሉ። ይህንንም ሲያብራሩ፣ “ከዚህ በፊት የስም ዝውውር ይሰጥበት በነበረው ‘ዞካ’ ሲስተም ሂደቶችን ጀምሬ በመሐል አገልግሎቱ ተቋርጦ ቆይቶ አሁን በአዲስ ሲስተም አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ነገር ግን አገልግሎቱ አርኪ አይደለም። በአሮጌው ሲስተም የስም ዝውውር ለማድረግ በተለያየ ሰው የቴሌብር አካውንት ለስም ዝውውር የፈፀምኳቸው ክፍያዎች የነበሩ ቢሆንም አሁን በአዲሱ ሲስተም መካተት አልቻሉም፡፡ የከፈልኩበትን ደረሰኝ እንደገና እንዳመጣም ተጠይቄያለሁ” ሲሉ በአገልግሎቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳዊት ሀይሌ በየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት፣ በተቋሙ ሁሉም አገልግሎት በኦንላይን እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ ገፀ ድር በመግባት በመመዝገብና ማመልከቻ ማቅረብ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ አቅመ ደካማና ኢንተርኔት ቤት ከፍለው መመዝገብ የማይችሉ ተገልጋዮችም በቢሮው ተመዝግበው የአገልግሎቱን ሂደት በስልክ መልእክት እየተላከላቸው ይከታተላሉ፡፡ የአገልግሎት ክፍያ፣ የመሀንዲስ ቀጠሮ፣ ያልተያያዘ ወይም የጎደለ ሰነድ ካለና ተቀባይነት ከሌለው እንዲሁም ሌሎች ሂደቶች በስልክ መልእክት ይደርሳቸዋል፡፡

አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ በመሰጠቱ በማንዋል ይሰጥ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው አቶ ዳዊት ያስረዳሉ፡፡ የሌብነትና የሰነድ መጥፋት ችግርን ይቀርፋል፡፡ በሲስተም በመሆኑ የወረቀት ምልልስን አስቀርቷል፤ ምክንያቱም ፋይሎች ስካን ተደርገው ገብተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የመሬት ነክ አገልግሎቶች ሲሰጡ የነበረው “ዞካ” በተሰኘ ተቋም የለማ ነበር፡፡ ከሁለት ወር በፊት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለማው ሲስተም አገልግሎት መሰጠት ጀምሯል፡፡

በአዲሱ ሲስተም ኢ-ካርታ ለመውሰድ 15 ቀን ወይም በዛ ቢባል 20 ቀን ብቻ ነው የሚወስደው። ከዚህ በፊት ግን ተደጋጋሚ የሲስተም መቆራረጥ ያጋጥም ነበር፡፡ ለአንድ ቀን ብቻ ሳይሆን አንድ ወር ድረስ ሲስተም ተቋርጦ የሚቆይበት ጊዜ ነበር፡፡ አዲሱ ሲስተም ከተጀመረ በኋላ የሲስተም መቆራረጥም ሆነ መዘግየት እንደሌለ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ ከስም ዝውውር አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከተገልጋይ የተነሳውን ችግር በተመለከተም፣ አንዳንድ ተገልጋዮች በአሮጌው ሲስተም ኢ-ካርታ ለማግኘት ክፍያ ፈፅመው ሊወስዱ ሲሉ ነው ሲስተሙ የተቋረጠው፡፡ እነዚህ ተገልጋዮች የከፈሉበትን ደረሰኞች ይዘው በመምጣት አዲሱ ሲስተም ላይ መረጃቸው እንዲያያዝ ይደረጋል፤ ሁለተኛ ክፍያም አይከፍሉም ብለዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ተገኝ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር አገልግሎቶችን ለማዘመን በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የለማው ሲስተም ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። አዲሱ ሲስተም ወደ ስራ ከገባ አንድ ወር የሞላው ሲሆን ረጅም ጊዜ ሲወስዱ የነበሩ አሰራሮችንና አገልግሎቶችን በማሳጠር ባለጉዳዮች በአጭር ጊዜ አገልግሎቱን እንዲያገኙ አስችሏል።

ለምሳሌ፡- የኢ-ካርታ አገልግሎት ባለጉዳዮች ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ የመረጃ ስህተት እንዳያጋጥም የተሰራውን ኢ-ካርታ መጨረሻ ላይ ትክክል መሆን አለመሆኑን እንዲያዩት ተደርጎ ታትሞ ይሰጣቸዋል። ከዚህ በፊት ግን ባለጉዳዮች ‘ካርታው ላይ እንዲህ ዓይነት ችግሮች አሉ፤ አልተስተካከለም’ በሚል ይመላለሱ ነበር፡፡ አዲሱ ሲስተም ይህን በመቅረፍ ቀልጣፋ አገልግሎትና ብዙ ተገልጋዮችን ማስተናገድ አስችሏል፡፡ ባለጉዳዮች አገልግሎት ለማግኘት በኦንላይን ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ በማግስቱ በሲስተም መጫን የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ለምሳሌ የኢ-ካርታ አገልግሎት ከዚህ ቀደም አንድ ወርና ከዚያ በላይ ጊዜ ይወሰዳል፡፡ በአዲሱ ሲስተም ባለጉዳዮች መረጃዎችን ካሟሉ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገልግሎት እንደሚያገኙ አቶ መልካሙ ተናግረዋል፡፡ ከስም ዝውውር ጋር በተያያዘ አንድ ተገልጋይ ያነሱትን ጥያቄ በተመለከተ አቶ መልካሙ ሲመልሱ፤ ተገልጋዩ በቀድሞ ሲስተም ክፍያ ከፈፀሙ ድጋሜ እንዲከፍሉ አይጠየቁም፤ በቴክኒክ ረገድ የገጠማቸው ችግር ካለም እንደሚታይና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል፡፡ ከሲስተም መዘግየት ጋር በተያያዘም ሲስተሙ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አቶ መልካሙ አንስተዋል፡፡ ፋይል ወደ ሲስተም መጫን (upload) ወራትን ይወስድ የነበረው በአዲሱ ሲስተም ግን በአንድ ወር ጊዜ በመጫን ወደ ባለሙያዎች እንዲደርስ እና ተገልጋዮች አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን አቶ መልካሙ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ተቋማት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በማዕከል ደረጃ ከሚሰጠው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተጨማሪ በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ተጨማሪ ቅርንጫፍ በመክፈት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሰጠ ነው፡፡ እነዚህን ለአብነት አነሳን እንጂ እንደ ንግድ ቢሮ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች በርካታ ተቋማት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በመስጠት የተገልጋዮችን እንግልትና እሮሮ መቀነስ እንደተቻለ ለዝግጅት ክፍላችን በተለያየ ጊዜ አስተያየታቸውን ከሰጡ ተገልጋዮች መረዳት ይቻላል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምን ይላል?

በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ተቋማት ፈጣን፣ ቀልጣፋና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ በመታገዝ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወነ ስራ 347 አገልግሎቶችን በኦንላይን መስጠት ተችሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 107 የሚሆኑት በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በኩል እየተሰጡ እንደሚገኙ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አዋሌ መሀመድ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያዘምኑ ሲስተሞችን በውስጥ አቅምና በውጭ በማልማት ወደ ስራ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል፡፡ ህዝብ እሮሮ ያቀርብባቸው የነበሩ እንደ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የንግድ ቢሮ፣ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የከነማ ፋርማሲ ያሉ ወደ ሰባት የሚደርሱ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በቴክኖሎጂ በመታገዝ አገልግሎት የሚሰጥበት ስርዓት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ተገልጋዮች አገልግሎት ለማግኘት ያባክኑት የነበረውን ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡ ለምሳሌ፡- ቀናትን ይፈጅ የነበረው የመታወቂያ አገልግሎት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መስጠት ተችሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ተገልጋዮች ወደ ቢሮ ሳይመጡ ቤት ድረስ አገልግሎቱን የሚያገኙበት ስርዓት ለመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን የቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የመሬትና አስተዳደር ቢሮ በቅርቡ ወደ ስራ የገባው ሲስተምም ምልልስን በመቀነስ፣ አገልግሎትን በአጭር ጊዜና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መስጠት እንዳስቻለ አቶ አዋሌ ይናገራሉ፡፡ በፊት በነበረው ሲስተም ካርታ ለማተም ረጅም ጊዜ የሚወስድና የሰው ንክኪውም ብዙ ነበር፡፡ አዲሱ ሲስተም ተገልጋዮች ቅድመ ሁኔታዎችን ካሟሉ በአጭር ጊዜ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ በመፍጠር ለተገልጋዮች እፎይታን ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ፡- መፍትሔ ሳያገኙ ለብዙ ጊዜ የቆዩ አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ማግኘት ችለዋል፡፡ የእዳ እገዳ አገልግሎት በደቂቃዎች መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

አዲሱ የመሬት ሲስተም የተገልጋዮች ፋይል፣ ይዞታቸው የሚገኝበት ቦታና ዝርዝር መረጃ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎችን አካትቶ የያዘ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአንዱ ይዞታ ሌላው ላይ ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለው ሲስተም ይህንን መቀበል የማይችል መሆኑን አቶ አዋሌ አብራርተዋል፡፡ ከሲስተም መዘግየትና መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ይታይ የነበረውን ችግር መቅረፍ እንደተቻለም አቶ አዋሌ ተናግረዋል። ለምሳሌ፡- ከዚህ ቀደም አንድ ካርታ ለማተም ብዙ ጊዜ ይወስድ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የሲቲኔት ኔትዎርክ መሰረተ ልማት ወደ ስራ በመግባቱ እና የባንድዊድዝ መጠንን በማሳደግ የመቆራረጥና መዘግየት ችግሩን ማቃለል መቻሉን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያቃልሉ ሲስተሞችን እያለሙ ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ በ2018 በጀት ዓመት በኢንዱስትሪ ቢሮ፣ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ በሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ በአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ በጤና ቢሮ፣ በትምህርትና ስልጠና ጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ በመሬት ልማትና አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቀላሉና ባጠረ ጊዜ ማግኘት የሚያስችሉ 18 ሲስተሞች በአምስት ወራት ለምተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ እነዚህ አገልግሎትን በማዘመንና እንግልትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አቅም መሆናቸውን አቶ አዋሌ አብራርተዋል፡፡

በስንታየሁምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review