ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ከሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ወደ አፍሪካ ተምሳሌትነት

You are currently viewing ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ከሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ወደ አፍሪካ ተምሳሌትነት

AMN- ታኅሣሥ 23/2018 ዓ/ም

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ከሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ወደ አፍሪካ ተምሳሌትነት ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አዋሌ ሞሐመድ ከኤ ም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ስርዓት አጠቃቀም ላይ ቀደም ሲል ሰዎች የነበራቸው ስጋት ተወግዶ ፣ አሁን ላይ የዲጂታል ክፍያ ዋነኛ መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል። ይህም ግልጸኝነትን ለማረጋገጥ እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ አክለዋል።

በዲጂታል 2025 የወረቀት ገንዘብ ማተሚያ ወጪን በመቀነስ የገንዘብ ፍሰቱ እንዲፈጥንና ኢኮኖሚው እንዲያድግ በማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል።

በሀገር ደረጃ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) ተቋም መቋቋሙ እና በኢንሳ በኩል የሚደረገው የቅድመ ደህንነት ክትትል የዲጂታል ስርዓቱን ከስጋት ነፃ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በ6ቱ የስማርት ሲቲ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ፣ በ2030 የውጭ ቴክኖሎጂን በማስቀረት በራስ አቅም ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ሥራ ለመስራት መታቀዱን አስታውቀዋል።

ስማርት ሲቲ ለመገንባት ስማርት ህዝብ ያስፈልጋል ያሉት አቶ አዋሌ ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከታቀደው በላይ መሳካቱን ገልጸው ይህም ወጣቶችና ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ሰፊ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው እያደረገ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን ለማሳካት የፈጠራና የፍጥነት ትስስር በመፍጠር ሁሉም ተቋማት በቅንጅት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review