ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ በከተማችን እየተገነቡ ከሚገኙ ስምንት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የቀበና እና የጊንፍሌ ወንዞችን የሥራ ሂደት ገምግመናል ብለዋል።
በእርግጥ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአገራችን አዲስ ተሞክሮ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂና ለውጥ አምጭ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም 19 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከእንጦጦ እስከ ካራማራ ድልድይ ድረስ የሚዘልቀው የቀበና ፕሮጀክት፣ ልክ እንደ እንጦጦና ፒኮክ ፓርኮች ሁሉ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ወደ መጠናቀቂያው ተቃርቧል ብለዋል።
ብክለት ተወግዶ፣ የአፈርና የሥነ-ምህዳር ጥበቃ ተደርጎላቸው፣ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን አጥተው የነበሩ ወንዞቻችን ታክመው ሲያንሰራሩ ማየት ትልቅ ስኬት ነው።
የደረቁ የውሃ ምንጮች እንደገና ሲፈልቁ፣ መጥፎ ሽታ ተወግዶ አካባቢው በአገር በቀል ዛፎች ተከቦ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጤናማና ንጹሕ አየር የሚተነፈስበት ማራኪ ገጽታ ሲላበስ ማየት የልፋታችን ትልቁ ውጤት ነው።

በዚህም የከተማችንን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጡ የውሃ ግድቦች፣ በርካታ ድልድዮች፣ ቼክ ዳሞች፣ ዘመናዊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የልጆች መጫወቻዎች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ሰፋፊ የመኪና ማቆሚያዎች ተገንብተዋል።
የከተማችንን ገጽታ የሚቀይሩ የአረንጓዴና የውበት ሥራዎችም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ።
ይህ ልማት በአሁኑ ወቅት ለሪል እስቴትና ለሆቴል አልሚዎች እጅግ አዋጭ የኢንቨስትመንት አካባቢ ፈጥሯል።
በመሆኑም፣ ዕውቀትና ገንዘብ ያላችሁ ባለሀብቶች በዚህ ልዩ የልማት ዕድል ላይ እንደወትሮው በንቃት እንድትሳተፉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም፤ ይህንን የትውልድ ኩራት የሆነ ፕሮጀክት ከውጥን እስከ ፍጻሜው እውን ለማድረግ ሌት ተቀን የደከማችሁ አመራሮችን፣ ኮንትራክተሮችን፣ ባለሞያዎችን፣ ኢንተርፕራይዞችንና የልማቱ ባለቤት የሆናችሁ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከልብ አመሰግናለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።