በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛዉ የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፉ ሁለት ሀገራትን ትናንት ምሽት ለይቷል፡፡ ዛሬ በሚከናወኑ ጨዋታዎች ደግሞ ቀሪ ሁለት ሀገራት ይለያሉ።
ምሽት 1 ሰዓት ላይ አልጄሪያ ከ ናይጄሪያ ግማሽ ፍጻሜውን ለመቀላቀል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱም ሀገራት የምድባቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፉ ሲሆኑ ናይጄሪያ በጥሎ ማለፉ ሞዛምቢክን አልጄሪያ ደግሞ ዲምክራቲክ ኮንጎ ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

ናይጄሪያ እና አልጄሪያ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የተገናኙት 2019 ላይ ነበር፡፡ ግብፅ ባሰናዳቸው በዚህ ውድድር ላይ በግማሽ ፍፃሜ ተገናኝተው አልጄሪያ በሪያድ ማህሬዝ አስደናቂ ቅጣት ምት ታግዛ 2ለ1 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
ሌላኛው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ግብፅ እና ኮትዲቫር ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ነዉ፡፡
ውድድሩን ሰባት ጊዜ በማሸነፍ የክብረወሰን ባለቤት የሆነችዉ ግብጽ በመድረኩ ከነገሰች 16 ዓመታት ያሳፈለች ሲሆን ወደ ውጤት ለመመለስ ጠንካራዋን ኮትዲቯርን ትገጥማለች፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኖቹ ኮትዲቯሮች በአንፃሩ ተከታታይ ዋንጫን ለማንሳት ከግብፅ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተገናኙት ካሜሩን ባሰናዳችው የ2021 ውድድር ላይ ነበር፡፡
በወቅቱ ግብፅ በመለያ ምት አሸንፋ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላ ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ ግን ኮትዲቯር የማሸነፍ ግምት አግኝታለች፡፡
የግብፅ አሰልጣኝ ሆሳም ሃሰን እንዲሁም የኮትዲቯር አሰልጣኝ ኤመርስ ፋኤ ከ20 ዓመታት በፊት በተጫዋችነት ዘመናቸው በተቃራኒ የመጫወት እድል ነበራቸው፡፡ ዛሬ ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን በአሰልጣኝነት ይመራሉ፡፡
በአልማዝ አዳነ
