ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የንጹህ ኃይል ቀጣናዊ ትስሰርን እያጠናከረች ነዉ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የንጹህ ኃይል ቀጣናዊ ትስሰርን እያጠናከረች ነዉ

AMN ጥር 4/ ቀን 2018

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የንጹህ ኃይል ቀጣናዊ ትስሰርን እያጠናከረች መሆኗ ተገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ “Powering Humanity: Renewable Energy for Shared Prosperity” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው 16ኛው የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ (IRENA) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር(ዶ/ር) በጉባዔው ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የምትጠቀመው ኃይል ከ98 በመቶ በላይ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ንጹህ ኃይል አከፋፋይ በመሆን ቀጣናውን ማስተሳሰሯን እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽካርካሪዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ በማገድ ከዓለም የመጀመሪያ መሆኗን አንስተዋል።

ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነፃ በሆነ መንገድ ለማምጣት የያዘችውን ግብ ስኬታማነት የሚያሳይና ለሌሎች ታዳጊ ሀገራትም እንደ ሞዴል የሚወሰድ ተሞክሮ መሆኑ አብራርተዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል እ.ኤ.አ በ2027 አዲስ አበባ የሚካሄደው 32ኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ ያላትን ግንባር ቀደም ሚና ከማጠናከር በዘለለ ለታዳጊ አገራት ፍትሐዊ የኃይል ሽግግር እንዲረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፎች እንዲሳለጡ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

አምባሳደሩ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት እና ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይቶቹ የኢትዮጵያን የታዳሽ ሃይል የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ማስፋፊያ እንዲሁም ለኮፕ32 ጉባኤ ስኬት ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ ያተኮሩ መሆናቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review