AMN ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ 8 አጀንዳዎችን ይፋ አድርጓል::
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ይፋ ያደረጋቸው ስምንቱ አጀንዳዎች የኢትዮጵያዊያን ድምጽ፣ ቅሬታ፣ ተስፋ እና ፍላጎት ውጤት መሆናቸውን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ተናግረዋል።
ስምንቱ አጀንዳዎች ኮሚሽኑ ላለፉት አራት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ እና ከሀገር ውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያዊንን ባሳተፈ እና አካታች በሆነ መንገድ ያሰባሰባቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) የምክክሩ ስኬታማነት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።
ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ የህዝብ ወኪሎች፤ 130 ሚሊዮን ህዝብን እንደሚወክሉ በመገንዘብ የቀሩቡትን 8ቱን አጀንዳዎች በትኩርት እንዲመረምሩ እና እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ እክለውም በሚቀጥለው የምክክር ሂደት የወከላቸውን ህዝብ ሀሳብ በግልጽ በማሰማት ለሀገራዊ መግባባት የበኩላቸውን እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከፓርቲ ጥቅም በላይ ሀገራዊ መግባባትን እንዲያስቀድሙ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙሀን፣ ሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም ምሁራን በምክክር ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በትዝታ መንግስቱ