የእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ይከናወናል፡፡ ሁለቱ የለንደን ሃያል ክለቦች ቼልሲ እና አርሰናል በስታምፎርድ ብሪጅ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ቼልሲ በአዲሱ አሰልጣኝ ሊያም ሮሲኒኦር እየተመራ ሁለተኛ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ እንግሊዛዊው አሰልጣኝ በኤፍ ኤ ካፕ 3ኛ ዙር ጨዋታ ቻርልተንን 5ለ1 ማሸነፍ ችሏል፡፡
በቼልሲ በኩል አማካዩ ሞይሰስ ካይሴዶ በቅጣት አይሰለፍም፡፡ ከዚህ ውጪ በቡድኑ ውስጥ አዲስ የጉዳት ዜና እንደሌለ አሰልጣኙ ከጨዋታው በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልጿል፡፡
በአራት ውድድር ላይ ጥሩ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አርሰናል ተከላካዮቹ ሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ፒዬሮ ሂንካፒዬን በጉዳት ያጣል፡፡ ሌላኛው ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ እና ሊአንድሮ ትሮሳርድም በጨዋታው ላይሳተፉ እንደሚችሉ ሚካኤል አርቴታ ተናግሯል፡፡
ስፔናዊው አሰልጣኝ በኤፍ ኤ ካፕ ፖርትስማውዝን ሲያሸንፍ ብዙ እድል የማያገኙ ተጫዋቾችን ተጠቅሞ ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ ግን ወደ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ፊቱን ያዞራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች በቅርብ ዓመታት ባከናወኗቸው ጨዋታዎች መድፈኞቹ የበላይነቱን ይወስዳሉ፡፡ የለንደን ኩራት እኔ ነኝ የሚለው ቼልሲ በሁሉም ውድድሮች ከአርሰናል ጋር ካደረጋቸው የመጨረሻ ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው፡፡ አርሰናል አምስቱን አሸንፏል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት እና 1ለ1 በተለያዩበት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ቼልሲ አስደናቂ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ ሞይሰስ ካይሴዶን በቀይ ካርድ ባጣበት ጨዋታ 1ለ1 መለያየቱ ይታወሳል፡፡
የዛሬው የካራባኦ ካፕ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት ይጀምራል፡፡ ሳይመን ሁፐር ደግሞ በዋና ዳኝነት ይመሩታል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ