AMN ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
አፍሪካ በአለም መድረክ የሚገባትን ዉክልና እንድታገኝ ኢትዮጵያ የማያቋርጥ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነዉ፡፡
ይህ መድረክ የአፍሪካ ሀገራት በጋራ አጀንዳዎች ላይ በጥልቀት በመምከር የጋራ አቋምን እንዲያራምዱ የሚያግዛቸዉ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የአለም አሰላለፍ እና ፍጥነት ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚቃኝ እና ተለዋዋጭ ነዉ ያሉት ዶ/ር ጌድዮን የአፍሪካ ሀገራት በመከባበር ላይ የተመሰረተ እና በጋራ ተጠቃማነት ላይ ያተኮረ አካሄድን ሊከተሉ ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካ ዘመኑን በዋጀ እሳቤ በአለም ላይ ዉክልናን ለማግኘት ሀገራቱ በትብብር፤ በእቅድ እና በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ግብን እዉን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ እድገት በአፍሪካ የሚዘወር የአፍሪካ ሀብትም ለአፍሪካ ልማት እንድዉል ማድረግ ይጠበቃል ነዉ ያሉት፡፡
በተመስገን ይመር