AMN ጥር 15 /2018
ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል እና በጅቡቲ የሰሜን ምዕራብ ግንባር አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሸህሚ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል የኢትዮጵያና የጅቡቲ ወታደራዊ አመራሮች ወታደራዊ ግንኙነት ጠንካራ እና ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
ትብብሩ አካባቢውን ከወንጀለኞች እና ህገወጥ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ታጣቂዎችን በጋራ በመከላከል ረገድ የቆየና ታሪካዊ አውድ ያለው እንደሆነ አመልክተዋል።
ከአንድ አመት በፊትም በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ተገኝተው ወታደራዊ ቅኝት ማድረጋቸውን ያወሱት ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል በወቅቱ የተጀመረው የትብብር ማዕቀፍ ተጠናክሮ በመቀጠሉ አሁን ለተካሄደው ወታደራዊ ስምምነት ፈር ቀዳጅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዋና አዛዡ በቀጣይም አዳዲስ ስምምነቶችን በመጨመርና በመከለስ አስፈላጊው ወታደራዊ ትብብር የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ሜጀር ጀኔራል ተስፋየ ወልደ ማርያም በበኩላቸው በቀጠናው በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች በዋና ዋና የጋራ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሀገር እና በተቋም ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች ተገቢውን አፈፃፀም የሚያገኙት በቀጠናው የሚገኙት ወታደራዊ አመራሮች በሚያደርጉት የተጠናከረ ግንኙነት በመሆኑ አሁን በዚህ ቦታ የምናደርገው ውይይትና ስምምነት የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድገው ነው ብለዋል።
የጅቡቲ ሰሜን ምዕራብ ግንባር አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሸህሚም የጅቡቲ ወታደራዊ ኃይል ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለው አውስተዋል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ወይይቶችና ስምምነቶች በሁለቱ ሀገራት ድንበር የሚከሰቱ የተለያዩ ወንጀሎችን በጋራ እና በመግባባት መከላከልና ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደውና መግባባት ላይ በተደረሰበት ውይይትም በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል መዋቅርን ማቋቋም፣ ወቅታዊና ደህንነቱ የተጠበቀ መረጃ መለዋወጥ፣ ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል እና ሌሎች ሀሳቦች ተነስተዋል።
በውይይቱም የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ በጅቡቲ፣ ከሰላም አስከባሪ ቢሮ ጄኔራል መኮንኖችና ከፌደራል ፖሊስ አመራሮች መገኘታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።