AMN-ጥር 15/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያለ ቅጣት የሚከናወነው የንግድ ሥራ ፈቃድ የዕድሳት ጊዜ ለተጨማሪ 15 ቀናት መራዘሙን አስታወቀ።
በዚህም መሠረት የንግዱ ማህበረሰብ እስከ ጥር 30/2018 ዓ.ም ድረስ ያለ ምንም ቅጣት ፈቃዳቸውን ማደስ እንደሚችሉ ተገልጿል።
እንደ ቢሮው መግለጫ ከሆነ፣ ቀደም ሲል እስከ ታህሳስ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ተወስኖ የነበረው የዕድሳት ጊዜ ለ15 ቀናት ተራዝሞ የቆየ ቢሆንም፣ አሁንም ዕድሳታቸውን ያላጠናቀቁ ነጋዴዎች በመኖራቸው ለሁለተኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲራዘም ተወስኗል።
ለቀኑ መራዘም ዋናው ምክንያት ነጋዴዎች የግብር ክሊራንስ በማግኘት ሂደት ላይ የታዩ መጓተቶችን በመጥቀስ ላቀረቡት ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት መሆኑ ታውቋል።
ቅሬታው በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ነጋዴዎች ያሉባቸውን ችግሮች ፈትተው እንዲያሳድሱ ዕድል ተሰጥቷል።
የንግድ ሥራ ፈቃድ ዕድሳቱ በኦንላይን እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ አገልግሎቱ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል።
ይህ የማራዘሚያ ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠ ሲሆን፣ የንግዱ ማህበረሰብ በተቀመጠው አዲሱ የጊዜ ገደብ ማለትም እስከ ጥር 30/2018 ዓ.ም ድረስ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ ጥሪ ማቅረቡን ቢሮው ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡