“የህፃናት ማቆያው ያለስጋት ስራዬን ለመስራት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልኛል”
ወይዘሮ ድርቤ ብርሀኑ
“አይደለም ስራዬን በውጤታማነት መስራት ይቅርና ለመልቀቅ ጫፍ ላይ ደርሼ ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጄን የሚይዝልኝ ሰው አልነበረኝም፡፡ ቆየት ብሎ ደግሞ ስራዬን ከምለቅ እህቴ ቤት አስቀምጬ ብሰራ የሚል ሀሳብ መጥቶልኝ ሰፈር ለቅቄ በውድ ዋጋ ለመከራየት ተገደድኩ፡፡ ይህም ሆኖ ቤት አስቀምጬ ወደ ስራ ቦታ በምመጣበት ወቅት ውስጤ በጣም ይጨነቅ ስለነበር ተረጋግቼ በውጤታማነት ለመስራት እቸገር ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጠዋት ላይ አረፍድ ነበር፡፡ ይህም የተመደብኩበትን ስራ በውጤታማነት እንዳልሰራ ያደርገኝ ነበር፤ በዚህም በጣም እሳቀቅ ነበር፡፡
በቢሮዬ የህጻናት መዋያ ከተቋቋመ በኋላ ግን በልጄና በራሴ ላይ ከፈጠረው ሰላም ባለፈ ስራዬን ያለሀሳብና ጭንቀት እንድሰራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልኛል፡፡ በምሰራበት መስሪያ ቤት በዚህ መልኩ በተመቻቸና ንጽህናው በተጠበቀ የህጻናት መዋያ ልጄ እንክብካቤ እያገኘ መዋሉ በስራዬ ላይ ደስተኛ ሆኜ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ ማርፈድ ቀርቷል” ሲሉ አስተያየታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ያጋሩት በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የግዢ ባለሙያ ወይዘሮ ድርቤ ብርሀኑ ናቸው፡፡
“በመስሪያ ቤቴ የህጻናት ማቆያ ስላልነበረ የመጀመሪያ ልጄን ያሳደግኩት በከባድ ድካም ውስጥ ነው” የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሪፎርም ባለሙያ ወይዘሮ ብሬ ግርማ ናቸው። “በቤቴ ልጄን የሚይዝልኝ ስላልነበረ በሌሊት ተነስቼ እናቴ ወዳለችበት አካባቢ አድርሼ ነበር ወደስራ የምገባው፡፡ በዚህ ምክንያት ስራ ላይ አንቀላፋ እንዲሁም ይደክመኝ ነበር፡፡ በተጨማሪም ልጄ የሚውልበት ስፍራ ከስራ ቦታዬ የራቀ በመሆኑ አንዳንዴ ሲታመም በመጨናነቅ ቶሎ ቶሎ ስልክ በመደወል ነበር ጊዜዬን የማሳልፈው፡፡ በአብዛኛው ጠዋት ማርፈድ አንዲሁም ማታ ሰዓት ሳይደርስ ቀድሞ የመውጣት ችግር ነበረብኝ። ይህም ለስራዬ እንቅፋት ሆኖብኝ ቆይቷል፡፡

ሁለተኛ ልጄን ስወልድ ግን የቢሮው የህጻናት ማቆያ ስራ ጀምሯል፡፡ ይህም ስራዬን ያለምንም ሰዓት መሸራረፍ እንዳከናውን አድርጎኛል፡፡ አሁን ላይ በመጀመሪያ ልጄ ያየሁት ሁሉ ችግር ተቃሏል፡፡ ማርፈድ፣ መቅረት የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሰቀቀን፣ ከጭንቀት ነጻ ወጥቻለሁ፡፡ ሌሊት ተነስቼ ስራ ቦታ ለመድረስ መሯሯጥ የለም፡፡ ልጄን አዝየ እንደማንኛውም ሰራተኛ ጠዋት እኩል እገባለሁ፤ ማታም እወጣለሁ፡፡ በተለይም ጠዋት እዛው ቢሮዬ በሚገኘው ማቆያ ውስጥ ልጄን አብልቼና አጠጥቼ ስራ ገበታ ላይ በሰዓት እገኛለሁ፡፡ ታመመ እንኳን ብለው ቢጠሩኝ እዛው ስለሆነ በቅርበት አይቼ ወደ ስራዬ እመለሳለሁ። ልጄ የሚውልበት ስፍራ ምቹ በመሆኑ ሙሉ የስራ ሰዓቴን ስራ ላይ ማዋል ችያለሁ፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ” ሲሉም አክለዋል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፎዝያ ኡመር በአለማያ የመጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሙያ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የአንድ ዓመት ከ6 ወር ልጃቸውን በትምህርት ቤቱ ማቆያ ያስገቡት የ7 ወር ህጻን እያለች ነው፡፡ አሁን ካለው የኑሮ ሲፈጸሙ የሚስተዋሉ ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ድርጊቶች ልጅን አምኖ ትቶ ወደ ስራ ለመሄድ ከባድ ያደርገዋል፡፡ በትምህርት ቤታቸው የህጻናት ማቆያ ባይኖር በስራቸው ላይም ሆነ አጠቃላይ በኑሯቸው ላይ ከባድ ጫና ሊፈጠርባቸው እንደሚችል አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ከመምህርት በተጓዳኝ የኮሌጅ ተማሪ በመሆናቸው ማቆያ ከማስገባታቸው በፊት ለአንድ ወር ያህል ልጃቸውን አዝለው ይንቀሳቀሱ እንደነበርና ልጅ ይዞ መማርም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ ለማስፈጸም ምን ያህል ይከብድ እንደነበር ካሳለፉት ገጠመኝ ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ቀኑን ሙሉ ማስተማር ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚናገሩት፡፡ ምክንያቱም ማስተማር በቂ ዝግጅት ማድረግን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ልጅ አዝሎ ማስተማር ስለማይቻል በሚሰሩበት ትምህርት ቤት መዋያ ባይኖር ስራቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ብርቱካን በቀለ በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የግዢ ቡድን መሪ ናቸው፡፡ የህጻናት መዋያ የመንግስት ስራ ሰዓት እንዳይበደል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአብዛኛው አጥቢ እናቶች “ልጄ ታመመ/ ታመመች፣ ምግብ ላዘጋጅ ነው፣ ሰራተኛ ወጣብኝ በሚሉና መሰል ምክንያቶች ያረፍዱና ይቀሩ ነበር፡፡ ማታ ላይም መውጫ ሰዓት ሳይደርስ ወደ ቤት ይሄዳሉ፡፡ አእምሯቸው ያለው ስራ ላይ ሳይሆን ልጆቻቸው ላይ ነበር፡፡ ብዙ ሰዓታቸውን ስልክ በመደወል ያሳልፉ ነበር፡፡ ስራ እስከመተው የደረሱ እናቶች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚያረፍዱና የሚቀሩ ሴት ሰራተኞችን ስራ ለመሸፈን ጥረት በሚያደርጉ ሌሎች ሰራተኞች ላይም ጫና ይፈጥር ነበር፡፡

አሁን ግን ልጆቻቸውን በስራ ቦታቸው ይዘው በመምጣት በቅርበት እያጠቡ፣ እያዩ እንዲሰሩ በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ሳያረፍዱና ሳይቀሩ፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ስራ ላይ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ ችግር ቢፈጠር እንኳን ምንም ሳይደናገጡ በቅርበት ፈትተው ቶሎ ወደ ስራ ይመለሳሉ፡፡ ይህም ስራቸው ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ አድርጓቸዋል፡፡ የመንግስት ሴት ሰራተኞች ልጆቻቸው ምን ይሆኑብናል ብለው ሳይቸገሩ እፎይ ብለው እንዲሰሩም ሆነ የመንግስት የስራ ሰዓት እንዳይበደል መንግስት ያመቻቸው የህጻናት መዋያ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉም ቡድን መሪዋ ወይዘሮ ብርቱካን አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ ሰላማዊት እውነቱ በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በቀዳማይ ልጅነት እድገትና የቀን ማቆያ ማእከላት ማስፋፋትና ማደራጀት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሴክተር መስሪያ ቤቶች የህጻናት የቀን ማቆያ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የህጻናት የቀን ማቆያ፣ ሙሉ ወጪው በመንግስት የሚደገፍ የህጻናት የቀን ማቆያ እና እናቶች የህጻናት የቀን ማቆያን ጨምሮ 833 ማእከላት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእነዚህ የቀን ህጻናት ማቆያ ማእከላት 13 ሺህ 380 ህጻናት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ተቋማት የቀን ህጻናት ማቆያ ማእከላት እንዲቋቋም መመሪያ ወርዷል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ያቋቁማሉ ተብለው የተያዙት 12 ሴክተሮች ናቸው፡፡ ሰባቱ የወረዳ መዋቅሮች ሲሆኑ አምስቱ የልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ በወረዳ መዋቅሮች ከሚቋቋሙት ሰባቱ የቀን ማቆያዎች መካከል ስድስቱ አቋቁመዋል፡፡ አንዱ በግንባታ ሂደት ላይ ነው፡፡ የልማት ድርጅቶችም መዋያ እንዲያቋቁሙ ቢሮው በአካል በመሄድና ውይይት በማድረግ በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ስምምነት ላይ በመድረስ፤ በዚህም ካሉት ዘጠኝ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ሶስቱ የሞግዚት ቅጥር ላይ ሲሆኑ ስድስቱ የቦታ ልየታ ላይ ናቸው፡፡ የህጻናት የቀን መዋያ የሌላቸው ተቋማት እንዲያቋቁሙ ቢሮው በየጊዜው ግፊት የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡
የህጻናት የቀን መዋያ በሴክተር መስሪያ ቤቶች ከተቋቋመ በኋላ ከሴቶችና ከህጻናት አኳያ ስላመጣው ለውጥ ቢሮው ከኢትዮጵያ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ጥናት አደርጓል፡፡ ጥናቱ ይፋ ባይደረግም 67 በመቶ ሴቶች ስራ ላይ ያላቸው አፈጻጸም እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ሴቶች በስራ ገበታቸው ተረጋግተው እንዲቆዩ በማደረግ ረገድ ያለው አበርክቶም 59 በመቶ ደርሷል። ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ፖሊስ መምሪያዎችና ሁሉም ማቋቋም አለባቸው፡፡ ያላቋቋሙ በዚህ ዓመት የግዴታ ማቋቋም እንዳለባቸው ግፊት እየተደረገ ነው፡፡ ቢሮው የክትትልና ድጋፍ ባለሙያዎችንም አሰማርቷል። እንደከተማ ምን ያህል ትምህርት ቤቶች እንዳሉና ከነዚህም ውስጥ ምን ያህሎቹ አቋቁመዋል? ካላቋቋሙ ምክንያታቸው ምንድነው? ቀጣይ ለማቋቋም ምን አስበዋል? የሚለውን ለማወቅ ባለሙያዎቹ ተመድበው እየሰሩ እንደሚገኙና በቀጣይ በሁሉም ተቋማት እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ እንደሚወሰድ ነው የቡድን መሪዋ ወይዘሮ ሰላማዊት የገለፁት፡፡
በለይላ መሀመድ