AMN – ጥር 17/ 2018 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን 90ኛ ዓመት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሀገሪቱን የአየር ላይ የመከላከል አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ግልጽ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
አየር ኃይሉ 90 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም በዕድሜው ልክ ተከታታይ ግንባታ ሳይደረግለት መቆየቱን እና ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 85 ዓመታት ሙሉ ከተከናወነው ሥራ ጋር የሚመጣጠን የቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ግንባታ መተግበሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፤ ይህም ኢትዮጵያን ከአየር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን የመታጠቅና የብቃት ደረጃን ከፍ የማድረግ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት የአየር ኃይሉን አቅም ለማሳደግ በጀትና የኃይል ምንጭ ለይቶ ከዋና ዋና አምራቾች ጋር በትብብር መሥራት መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት የአራተኛው ትውልድ (4th Generation) የመዋጋት ብቃት የገነባው አየር ኃይል፣ በ2030 ወደ አምስተኛው ትውልድ ይሸጋገራል ብለዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የአየር ኃይሉ የተቀናጀ አቅም አሁን ካለበት በእጥፍ እንዲያድግ የሚደረግ መሆኑን እና የተዋጊ አውሮፕላኖች ቁጥርም በተመሳሳይ መልኩ በእጥፍ እንደሚጨምር ገልጸዋል።
የሰው ሕይወትን በቴክኖሎጂ መተካት ያስፈለገው አዲሱ የጦርነት ስትራቴጂ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በዒላማው ላይ ትክክለኛነት ያለውና ውጊያን የሚያሳጥር መሆኑን ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውድ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰው ሕይወት መስዋዕትነትን በመቀነስ የሚፈለገውን ድል ለመጎናጸፍ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአየር ኃይሉ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚገነባ አረጋግጠዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ