7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈጊዉን ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን – ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

You are currently viewing 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን አስፈጊዉን ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን – ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ጥር 20 /2018

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ኤ ኤም ኤን (AMN) ከተለያዩ የፓርቲ አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።

ፓርቲዎቹ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ዕጩዎችን ከማስመዝገብ ባለፈ፣ ምርጫው ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ያላቸውን ዝግጅት አብራርተዋል።

የህዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኢንጂነር ሱራፌል እሸቱ ፤ ፓርቲው ከአባላቱ ጋር ሰፊ የመግባባት ስራ መሥራቱን የገለጹ ሲሆን ፤ በየክልሉ የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በጠቅላላ ጉባኤ በማጽደቅ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም የዕጩ ምዝገባ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ይህንን ትውልድ ሊመጥን የሚችል ፖሊሲና ፕሮግራም ይዘን ቀርበናል ያሉትኢንጂነር ሱራፌል ፤ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ጥረት እናደርጋለን።

የወሎ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው የምዝገባ ስራ እያከናወኑ መሆኑን እና አዲስ ምርጫ ተሳታፊ እንደመሆናቸው መጠን የዜጎችን ፎርም የማስሞላት ስራ ማጠናቀቃቸውንና አሁን ላይ የዕጩ ምዝገባ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በእነሱም ሆነ በገዥው ፓርቲ ዘንድ ታማኝነት ያለውና ህዝቡ ሙሉ በሙሉ የሚቀበለው የተሻለ ምርጫ እንዲሆን ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ የምዝገባ ሂደት ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት ለየት ያለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ክፍለማርያም፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መስፈርት መሠረት የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን በመጠቀም ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የስራ አስፈጻሚ አባልና የስትራቴጂክ ክፍል ኃላፊ አቶ ማሩ ጃኔ ደግሞ ስትራቴጂያዊ ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

ዕጩዎችን ከማስመዝገብ ባለፈ፣ በፓርቲው ውስጥ የተለያዩ ግምገማዎችን በማድረግ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አቶ ማሩ ገልጸዋል። ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ (Schedule) መሠረት ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ሀገርንና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሀገራዊ ጉዳዮችን ይዘው ለመቅረብ መዘጋጀታቸውን የገለጹት አመራሩ፣ ምርጫው አስቻይና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንደሚከናወን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review