አዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ያስተናገደቻቸው ከ150 በላይ ጉባኤዎች ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP 32) ለማስተናገድ በቂ አቅም እና ዝግጁነት እንዳላት አመላካች ነው ተብሏል።
የአማዞን ደን መግቢያ በር በመባል የምትታወቀውና በብራዚል ሰሜናዊ ግዛት የምትገኘው የቤሌም ከተማ የዓለምን ትኩረት የሳበችው በዝናባማ ሰማይ ስር በሚገኙት አስደናቂ ህንጻዎቿ ብቻ አይደለም። ‘የማንጎ ዛፎች ከተማ’ (The City of Mango Trees) በሚል ቅፅል ስም የምትጠራው ይህች ከተማ፣ በየጎዳናዎቿ ላይ እንደ አጥር ተሰድረው በሚገኙት ግዙፍ የማንጎ ዛፎች ሳቢያ ለእግረኞች ልዩ ፍቅር ትቸራለች። ይህም በተገባደደው የፈረንጆቹ ዓመት 30ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 30) ለማስተናገድ ታሪካዊ ዕድል አስገኝቶላታል።
ይህች ከተማ ግዙፉን ጉባኤ ስታስተናግድ፣ ከአማዞን ደን ጥበቃ ጎን ለጎን የከተማዋን ኢኮኖሚ ከደቃቅ ንግድ ወደ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከልነት አሸጋግራዋለች። ቤሌም ጉባኤውን በማስተናገዷ ያገኘችው ጥቅም የሚለካው በገንዘብ ብቻ አይደለም። በጉባኤው ዋዜማ የተገነቡት ዘመናዊ የውሃ ላይ ትራንስፖርቶች፣ የታደሱት ጥንታዊ ወደቦችና የተገነቡት በሺህ የሚቆጠሩ ሆቴሎች ለከተማዋ አዲስ ህይወት ዘርተውባታል። ዛሬ ላይ ቤሌም ስትታወስ የዓለም መሪዎች ስለተፈጥሮ ጥበቃ የተሟገቱባት ብቻ ሳትሆን፣ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተደማምረው ለዓለም ያስተዋወቋት ከተማ ሆና ነው፡፡
ይህ የቤሌም ስኬት ደግሞ ባለፉት 6 ወራት ከ150 በላይ ኮንፈረንሶችን በድል ላከናወነችውና የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን (COP 32ን) ለማስተናገድ በመዘጋጀት ላይ ለምትገኘው አዲስ አበባ ታላቅ ትምህርት የሚሰጥና የመንፈስ ስንቅ የሚሆን ነው። በእርግጥ መብራቶቿ በደመቁት፣ ኮሪደሮቿ በጸዱትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈሷ የታደሰው አዲስ አበባ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጣ ወደ ቤሌም አቅንታ የምትቀስመው ልምድ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን የደረሰችበት ደረጃም ቀላል አይደለም፡፡
አዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ150 በላይ ታላላቅ ኮንፈረንሶችን ማስተናገዷን የሚገልጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የከተማዋን አዲስ ምዕራፍ ዳግም ያበሰረና ትልቅ ልምድ የሚወሰድበት ሆኗል። ይህ ቁጥር ከተራ አኃዝ በላይ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ፣ መሠረተ-ልማት እና ዲፕሎማሲያዊ ዕድገት ለዓለም ያሳየበት ክስተት ነው።

አዲስ አበባ በዚህ ልክ የገዘፉ ሁነቶችን በስኬት ማስተናገዷ ምን አንድምታ አለው? የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማደግ ለከተማዋ የኢኮኖሚ ዋልታነት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ለታላቁ የአየር ንብረት ጉባኤ (COP 32) ዝግጅትስ ምን ዓይነት ልምድ ሊወሰድበት ይችላል? የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት ደግሞ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እንደሚያሳየው፣ ከተማዋ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ዘርፍ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት እያስመዘገበች ነው። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ150 በላይ ታላላቅ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፈረንሶች በከተማዋ ተካሂደዋል። ይህ ቁጥር ለከተማዋ የኢኮኖሚ እድገት፣ ለዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት እና ለወደፊት ግዙፍ ሁነቶች ያላትን ዝግጁነት ማሳያ ነው።
አንድ ከተማ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ማስተናገዷ ብዙ ትርጉሞች አሉት የሚሉት የሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ሞሪስ ሮቼ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2000 ባሳተሙት ‘Mega-Events and Modernity: Olympics and Expos in the Growth of Global Culture’ በተሰኘው የጥናት መጽሐፋቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኩነቶች ያላቸውን ትርጉም ሲያስረዱ፣ ከተሞች ስብሰባዎቹን ለማስተናገድ ሲሉ የሚያከናውኗቸው የግንባታ ሥራዎች ለከተማዋ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ሞተር ይሆናሉ ይላሉ፡፡
በሌላም በኩል ስብሰባዎችን ማስተናገድ ከተማዋ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተቀባይነትና ዝና እንደሚጨምርና የከተማዋን ነዋሪዎች ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር የሚያስተሳስር ባህላዊ ድልድይ ይሆናሉ ሲሉ ሞሪስ ሮቼ ያብራራሉ።
ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከመደበኛ ቱሪስት በአማካይ በሦስት እጥፍ ገብ እንድሚያስገኝ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህም ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት ዘርፍ፣ ለባህል አልባሳትና ለቅርስ መሸጫ መደብሮች ከፍተኛ ገቢ ያስገኛልና የሚፈጥረው የኢኮኖሚ መነቃቃት ቀላል አይሆንም። ኮንፈረንስ ቱሪዝም (MICE) ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡ ተጓዦች የሚሳተፉበት ዘርፍ ስለመሆኑም ሞሪስ ሮቼ ያስረዳሉ።

የቱሪዝም ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ እንደሚሉትም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አመርቂ ነው። የከተማዋን ገጽታ ማሻሻልና መዝናኛ ቦታዎች የሆኑት እንደ ሸገር ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ እና ወዳጅነት አደባባይ ያሉት ቦታዎች ለእንግዶች የመዝናኛና የመሰብሰቢያ ቦታ በመሆን ለጉባኤው ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።
የእነዚህን ቦታዎች ውበትና አገልግሎት ማሳደግ ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጡ ያበረታታል ሲሉም ይገልጻሉ። ኮንፈረንስ ቱሪዝም ከሚኖረው ቀጥተኛ ፋይዳ በተጨማሪ ሀገርን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
አንድን ከተማ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት የሚመርጡ አካላት መጀመሪያ የሚያዩት ዝግጁነትን ነው። አዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ያስተናገደቻቸው ከ150 በላይ ጉባኤዎች ከተማዋ አስተማማኝ የኢንተርኔት፣ የኤሌክትሪክ፣ የሆቴልና የደህንነት ዝግጁነት ደረጃ ላይ መድረሷን ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው። ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP 32) ለማስተናገድ የምታደርገው ዝግጅት፣ አሁን ካለው አፈፃፀም ትልቅ ግብዓት ያገኛል። በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን ከኤርፖርት እስከ ስብሰባ አዳራሽ የመምራት አቅም እየዳበረ ስለመምጣቱም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
አዲስ አበባ ባስተናገደቻቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ላይ የኮሪደር ልማት እንደ ‘ሞተር’ ሆኖ አገልግሏል። እንግዶች ከአዳራሽ ሲወጡ የሚንሸራሸሩባቸው ንጹህ መንገዶች፣ ብርሃናማ ምሽቶችና ዘመናዊ መናፈሻዎች መኖራቸው የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ያደርጋል።
ባለከፍተኛ ፍጥነት የኢንተርኔት አገልግሎት እና የዲጂታል ክፍያ ስርዓቶች (እንደ ኢ-ብር እና ቴሌብር) መስፋፋት እንግዶች ያለምንም እንግልት ግብይት እንዲፈጽሙ ረድቷል። ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP 32) ለማስተናገድ የተገኘውም ዕድል አሁን ባለው ስኬት ላይ የተገነባ ስለመሆኑ እሙን ነው።

ስኬቱ እንዳለ ሆኖ፣ አዲስ አበባ የዓለም ቁንጮ የኮንፈረንስ መዳረሻ ለመሆን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚኖርባት ባለሙያዎች ይመክራሉ። የጎንዮሽ ቱሪዝምን በማጠናከር ስብሰባ ጨርሰው የሚወጡ እንግዶች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚሄዱበትን ‘የዕለት ጉብኝት’ ፓኬጆችን ማስፋፋት ይገባል። የእንግዳ ተቀባይነት ዘርፉን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ፕሮቶኮል ማዘመን እና ለእንግዶች መረጃ የሚሰጡ ዲጂታል መተግበሪያዎችን በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚገባ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያው አቶ ሱራፌል ተክሉ ይገልጻሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP 32) ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ የዓለም መሪዎችን፣ ሳይንቲስቶችንና አክቲቪስቶችን በአንድ ከተማ የሚያገናኝ ግዙፍ ሁነት ነው። አዲስ አበባ ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመሸከም ያላትን ዝግጁነት በሦስት ዋና ዋና ማዕቀፎች መመልከት ይቻላል። የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ይበልጥ ማቀላጠፍ፣ የአየር መንገድ ትስስርን (Ethiopian Airlines) ከሆቴሎች ጋር በልዩ ፓኬጅ ማስተሳሰር እና የከተማዋን ታሪካዊ ስፍራዎች ለጎብኚዎች ምቹ በሆነ መልኩ በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል።
ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተርስ የተሰኘ ገጸ ድር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ዓለም በየዓመቱ ከምታሰናዳቸው ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ውስጥ አፍሪካ የምታዘጋጀው ከ3 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይሁንና የዓለም አቀፍ የማይስ (MICE) ኢንዱስትሪ ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ፣ እስከ 2032 ድረስም ወደ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል። ወሳኙ ጥያቄ ታዲያ በዘርፉ በስኬታማ ጎዳና ላይ ያለችው አዲስ አበባን ጨምሮ የአህጉሪቱ ከተሞች ከዚህ የመጪው ጊዜ ምንዳ እንዴት ሊቋደሱ ይገባል? የሚለው ይሆናል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ