በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብር መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከተሰናዱ መካከልም የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍት ውይይት እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
የባህል ፌስቲቫል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ ለ17ኛ ጊዜ የባህል ፌስቲቫል አዘጋጅቷል፡፡ ቢሮው የባህልን ልማታዊ አስተዋጽኦ በማጎልበት በየአመቱ በትኩረት ከሚያከናውናቸው ከተማ አቀፍ ሁነቶች መካከል አንዱ የሆነው አዲስ የባህል ፌስቲቫል በዚህ አመትም ለ17ኛ ጊዜ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፊታችን ሰኞ (ከጥር 23 እስከ 25/2018 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ገበያ ልማትና ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡ ፌስቲቫሉ የከተሜነት ባህልን፤ የስራ እና የጊዜ አጠቃቀምን፤ የአለባበስና የአመጋገብ ባህልን በማስተዋወቅ የመዲናዋን ገጽታ የሚገነባበት ከዛም አልፎ እንደ ገቢ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ነው ተብሏል፡፡
መጽሐፍት
“ሃያ ሦስት” መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ ከአሥር ዓመታት በፊት በመላው ዓለም በተለይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤንና ሐዘንን ፈጥሮ የነበረው የአይ.ኤስ.አይ.ኤስ (ISIS) የጭካኔ እርምጃ ሰለባ ከሆኑት መካከል ከሞት በተረፈ ወጣት የተዘጋጀ ነው። ዳንኤል አብርሃ ባዘጋጀው በዚህ መጽሐፍ፤ ከኢትዮጵያ ተነስቶ በሱዳንና በግብፅ በረሃዎች አቋርጦ ሊቢያ ድረስ የተጓዘበትን እጅግ አሰቃቂና ፈታኝ ጉዞ ይተርካል። መጽሐፉ በይዘት ደረጃ የጉዞ ማስታወሻ ሲሆን በ26 ምዕራፎች ተከፋፍሎና በ262 ገፆች ተቀንብቦ ለንባብ መብቃቱን የሁነት አዲስ መረጃ ያሳያል። ይህ መጽሐፍ በወቅቱ በሊቢያ በረሃ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች መታሰቢያ ከመሆኑም ባለፈ፣ የስደትን ገጽታን በአግባቡ መረዳት ለሚፈልጉ አንባቢያን ትልቅ ግብዓት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በተያያዘ መረጃ የደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል “የወዲያነሽ” መጽሐፍ በድጋሚ ታትሞ ለሽያጭ መቅረቡ ተገልጿል። መጽሐፉ ለረጅም ጊዜ ከገበያ ጠፍቶ የቆየ ቢሆንም፣ ከአንባቢያን እየቀረበ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት መሠረት በማድረግ በድጋሚ ታትሞ ለአንባቢያን እንዲደርስ ተደርጓል።
በሌላ መረጃ በዛሬው እለት በገጣሚና ደራሲ ታገል ሰይፉ መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ የነገረ መጻሕፍት መርሃ ግብር አካል በሆነው በዚህ ሁነት ደራሲው ታገል ሰይፉ በአካል በመገኘት ከአንባቢያን ጋር ውይይት ያደርጋል። የውይይቱ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር) ሲሆን መርሃ ግብሩ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ከቀበና፣ የካቶሊክ ኪዳነምሕረት ትምህርት ቤት አቅራቢያ፣ ወደ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት በሚወስደው መንገድ፣ ባማ አዲስ ሕንፃ አጠገብ፣ FSS አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
መጽሐፍትን ከተመለከተው መረጃ ሳንወጣ በዛሬው እለት ዋልያ የሐሳብ እና መጽሐፍ መድረክ ይካሄዳል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የፕሮጀክት መረጣን እና አፈጻጸምን መሰረት በማድረግ “ኑሮአችን ሁሉ ፕሮጀክት ነው” በሚል ርእስ ውይይት የሚደርግ ሲሆን የመነሻ ገለጻ አቶ ደረጄ ተክሌ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ ውይይቱ ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ 4 ኪሎ ኢክላስ ሕንፃ፣ ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ ይደረጋል፡፡
ፊልም
“ብሌን” የተሰኘ አዲስ ፊልም የምርቃት መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ፊልሙ ትናንትን ጨምሮ ዛሬ እና ነገ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች እየተመረቀ ነው፡፡ የፊልሙ ደራሲ ሙባረክ ያሲን ሲሆን አዘጋጁ ደግሞ ተዋናይ ሄኖክ ድንቁ ነው፡፡ በብሌን ፊልም ላይ ታምሩ ብርሃኑ፣ ካሳሁን ፍስሃ (ማንዴላ)፣ ሊና ካሳን ጨምሮ በርካታ አዳዲስና ታዋቂ አርቲስቶች ተውነውበታል፡፡
ሙዚቃ
“ስጦታ” አዲስ የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆነ፡፡ የድምጻዊ አዲስ ጉርሜሳ ይኸው አዲስ የሙዚቃ አልበም ትናንት አርብ በናሆም ሪከርድ አማካኝነት ለሙዚቃ ወዳጆች ደርሷል፡፡ አልበሙ 12 ያህል ሙዚቃዎችን የያዘው እና አንጋፋ እና ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን በፍቅር፣ በሠላም፣ በሀገር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ስራዎች ተካትተውበታል፡፡
በጊዜው አማረ