የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ
  • Post category:ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላንትናው ዕለት ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች፣ ሀገር ዐቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ውይይት አካሄደ።

የውይይቱን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫን “የቅድመ-ምርጫ” ዝግጅቱን የድኅረ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ ጥናት፤ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው የተለያዩ ውይይቶች የተገኙትን ግብዓቶች እንደ’መነሻ በመውሰድ፤ የሕግ ማሻሻያ በማፀደቅና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ባለድርሻ አካላትን አወያይቶ በማውጣት ጭምር የምርጫውን ነፃ፣ ተዓማኒና ዲሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉትን የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበር በዝርዝር አስረድተዋል።

የሰብሳቢዋን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ብሩክ የወንደሰን ቦርዱ ከክልል መንግሥታትና ከከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት የሰበሰበውን በአረንጓዴ፣ በቢጫና በቀይ የተፈረጀ የፀጥታ ሁኔታን በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን፤ የቀረበውን የፀጥታ ሁኔታ የሚያሳየውን መረጃ መሠረት አድርጎም ከተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥቶበታል።

ለተሰጡት አስተያየቶችም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች የከተማ አስተዳድር ከንቲባዎች እንዲሁም ከፀጥታ ተቋማት የመጡ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ቦርዱ እያከናወናቸው ባሉት የምርጫ የኦፕሬሽን ሥራዎችና አጠቃላይ ቦርዱን ለተመለከቱ አስተያየቶች ሜላትወርቅ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ ባለሞያው ብሩክ አስረድተዋል።

ሜላትወርቅ በመድረኩ የማጠቃለያ ንግግራቸው ከውይይት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል በማመን በውይይቱ ላይ የተሣተፉ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት፣ ሀገር ዐቀፍ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አመስግነው፤ በዕለቱ ከተደረገው ውይይት እንደተስተዋለው ውይይት የተለያዩ አስተሳሰቦችን ወደ አንድ በማምጣት ለአንድ ዐላማ “ዲሞክራሲያዊ ምርጫን” ለማስፈጸም ወደሚያስችል መግባባት እንደሚያመጣ መገንዘብ እንደሚቻል ተናግረዋል። ይኽ በፀጥታ ጉዳይ ላይ የተደረገ ውይይት የመጀመሪያ እንደሆነና በቀጣይም በፀጥታ ሁኔታም ሆነ አጠቃላይ በምርጫ ኦፕሬሽን ጉዳይ ላይ ተከታታይ ውይይቶች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review