የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥር 26/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዜጎች በኑሮ ውድነት የሚፈተኑባቸውን መሠረታዊ ዘርፎች በመለየት በረጅም ጊዜ ዕቅድ ለመቅረፍ ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ በተለይም በምግብ ዋስትና፣ በቤት ኪራይ ማረጋጋት፣ በትራንስፖርት እና በትምህርት ምገባ ዘርፎች ላይ የተጀመሩ ውጤታማ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለማቃለል በትኩረት እየሠራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካካል የምግብ ዋስትና እና የምገባ ማዕከላት ግንባታ አንዱ መሆኑን እና መንግስት ምግብን በበቂ ሁኔታ ለማምረትና ለማሠራጨት በከፍተኛ ፍጥነት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕዝብ የምግባ ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም የምግብ አቅርቦት የሚገኝባቸው ቦታዎች እንዲሰፉና ተደራሽነቱ እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

“ሰው የሚሰቃየው በቤት ኪራይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤቶችን አቅርቦት በተወሰነ ደረጃ በማሻሻልና የኪራይ ዋጋን በማረጋጋት ብዙ ዜጎችንና ሠራተኞችን ከችግር ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትራንስፖርትን ችግር ለመቅረፍ ወጪን ለመቀነስ በጋዝ የሚሰሩ አውቶቡሶችን የማምረትና የነበሩትን የመቀየር ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ሒደቱም ነባር የባስ ሞተሮችን ወደ ጋዝ የመቀየር ሥራ በአቃቂ የቴክኒክ ማዕከል እየተከናወነ እንደሚገኝ እና በቀጣዮቹ ስድስት ወራት አብዛኞቹ ተጠናቀው በቀጣይ ዓመት በአዲስ አበባ፣ ከዚያም ወደ ሌሎቹ የሀገሪቱ ክፍል አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤት ምገባ ማስፋፋት ሌላኛው የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራበት ያለ መሆኑን እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች በድህነት ምክንያት ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ እንዳያስቀሩ፣ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ይበልጥ እንደሚሰፋም አረጋግጠዋል።

መንግስት የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት እየሠራበት እንዳለ እና የዜጎች ገቢ ሊሻሻል የሚችለው አጠቃላይ ኢኮኖሚው ሲያድግ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ዘላቂ ሥራዎች አሁን ካለው የሪፎርም ሥራ ጋር ሲሰናሰሉ የዋጋ ግሽበት ፈተና በሒደት እየተቀረፈ እንደሚሔ ድ አስረድተዋል።

ያገኘነው ውጤት በጣም አስደናቂ ቢሆንም፣ የሚቀረው ሥራ ግን በጣም ብዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review