AMN የካቲት 03 ቀን 2018 ዓ.ም
19ኛው የራስ አልካይማህ ግማሽ ማራቶን በመጪው ቅዳሜ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ራስ አልካይማህ ከተማ ይደረጋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ደረጃ ከሰጣቸው የግማሽ ማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው አልካይማህ ለሚያሸንፍ አትሌት 20 ሺ ዶላር ሽልማት አዘጋጅቷል፡፡
ባለፈው ዓመት የተሳተፉት 10 ሺ 595 ተወዳዳሪዎች ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ውድድሩ እኤአ በ2007 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ያሸነፈው ሳሙኤል ዋንጂሩ የዓለም ፈጣን ሰዓትን አስመዝግቦበት ነበር፡፡ ካለፉት 18 ውድድሮች በወንዶች 13ቱን ኬንያውያን አትሌቶች ሲያሸንፉ አራቱ በኢትዮጵያውያኑ ድሪባ መርጋ ፣ ሌሊሳ ዴሲሳ ፣ ሞስነት ገረመውና ብርሃኑ ለገሰ አሸናፊነት ተጠናቀዋል፡፡
የመጀመሪያውን የሴቶች ውድድር ያሸነፈችው ብርሃኔ አደሬ ናት፡፡ ድሬ ቱኔ ፣ ሰንበሬ ተፈሪ ፣ እንዲሁም የ2022ቱን በ1፡04:14 ሰዓት አጠናቃ የቦታውን ክብረወሰን የሰበረችው ግርማዊት ገብረእግዚያብሄር ፣ ጽጌ ገብረሰላማና እጅጋየሁ ታዬ ሌሎች በራስ አልካይማህ ግማሽ ማራቶን ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው፡፡ የ2020ውን ውድድር ያሸነፈችው አባብል የሻነህ ቅዳሜ ትጠበቃለች፡፡

ከ19 ዓመቷ ጀምሮ በውድድር ላይ የምትገኘው አትሌት አባብል በፍቅረኛሞች ቀን በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚደረገውን ውድድር ለማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት አግኝታለች፡፡ አባብል ራስ አልካይማህ ላይ ከወንዶች ጋር በድብልቅ በመሮጥ የያዘችው ፈጣን ሰዓት በግርማዊት ገብረእግዚያብሄር ፣ ያለምዘርፍ የኋላውና ለተሰንበት ግደይ መሰበሩ የሚታወስ ነው፡፡
አባብል በ2020 በፖላንድ ጊድኒያ የተካሄደውን የዓለም የግማሽ ማራቶን ውድድር በበላይነት አጠናቃለች፡፡ አትሌቷ የቺካጎና ቦስተን ማራቶኖችን በሁለተኛነት እንዲሁም ኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶንን በሶስተኛነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም፡፡ አባብል በ2013ቱ የሞስኮ ዓለም ሻምፒዮና እና በ2016ቱ የሪዮ ዴጄኔሮ ኦሊምፒክ በ10 ሺ እና አምስት ሺ ሜትር ሀገሯን ወክላለች፡፡
ጎቲቶም ገብረስላሴ ባሸነፈችበት የ2022ቱ የዩጂን ዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን መወከሏ የሚታወስ ነው፡፡ አትሌት አባብል የቦነስ አይረስና ኢስታንቡል ግማሽ ማራቶኖችን በበላይነት ማጠናቀቀቋ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
የወንዶቹን ውድድር የሶስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮኑ ኬንያዊ ጂኦፍሬ ካምዎረር የማሸነፍ ቀዳሚ ግምት አግኝቷል፡፡ የ2013ቱን ውድድር ያሸነፈው ካምዎረር የኒው ዮርክ ማራቶንን ሁለት ጊዜ ያሸነፈ ስኬታማ አትሌት ነው፡፡
በታምራት አበራ