AMN – ሰኔ 30/2018 ዓ.ም
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግልና በተፎካካሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ሆነው ላገለገሉ በአዲሱ ምክር ቤት ለማይቀጥሉ የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ ከመንግስት ጋር ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በጋራ እንስራ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት እየተካሄደ ባለው 6ኛው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው፡፡
የግልና የተፎካካሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ባለፉት 5 ዓመታት በዕውቀታችሁ፣ በዓቅማችሁ እንዲሁም በመሻታችሁ ልክ ሀገራችሁን ያገለገላቸሁ፣ በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ድምፃቸሁን ያሰማችሁ፣ የህዝብን ጥያቄ፣የፓርቲ እና የኛ አመለካከት ብላችሁ ላራመዳችሁት ሃሳብ በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶቻችሁ በሚቀጥለው ምክር ቤት ባትቀጥሉም ከምክር ቤት ውጭ ከመንግስታችን ጋር በጋራ ሆነን ኢትዮጵያን እንድናገለግል ሲሉ በምክር ቤቱ ፊት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስታችን አናንተን አካቶ ኢትዮጵያን ማገልገል ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ የጋራ ሀገራችን ናት እኛም፣ እናንተም ልጆቿ በምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በተለያየ ዘርፍ ተባብረን ኢትዮጵያን እናበለጽግ፣ አብረን እንሥራ በማለትም አክለዋል፡፡
በያለው ጌታነህ