AMN የካቲት 04 / 2018 ዓ/ም
በ300 ሺህ ብር የሙስና ወንጀል የተጠረጠረን የመንግስት የስራ ኃላፊና በንግድ ስራ ላይ የተሰማራን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪዎች አቶ ዓለም ተ/ኃማኖት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የግዢ ቡድን መሪ እና አቶ ሳሙኤል መላኩ የተባሉ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ ሲሆኑ አቶ ዓለም ተ/ኃይማኖት በቢሮአቸው ለሚፈፀመው የችግኝ ጣቢያ ግብዓቶች ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ/ም በወጣ ጨረታ አቶ ሳሙኤል መላኩ ጨረታውን አሸንፈዋል፡፡

ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል መላኩም ከአቶ ዓለም ተ/ኃይማኖት ጋር በቀጣይ በቢሮው በሚቀርቡ የግዢ ሂደቶችና ጨረታዎች ላይ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ያልተገባን ድርድር በማድረግ ለቢሮው ግዢ ቡድን መሪ የሦስት መቶ ሺህ ብር ቼክ በሚሰጡበት ወቅት አስቀድሞ በየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክትትና የምርመራ ቡድን ጥናት ሲደረግባቸው በመቆየቱ ዛሬ የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ/ም እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡
ህብረተሰቡ መሰል የግዢ ስርዓቶችን ሲያከናውን ህጋዊ መንገድን መጠቀም እንዳለበት ያሳሰበው ፖሊስ የነጋዴው ማህበረሰብም መብቱን በገንዘብ ሊገዛ እንደማይገባም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡