AMN ግንቦት 22/2018

7ተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉ የአፍሪካ ህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ።
የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ (AUEOM) መሪ የሆኑት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።
ኡሁሩ ኬንያታ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር መለስ አለም አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የታዛቢ ቡድን መሪው ኡሁሩ ኬንያታ እንደገለጹት፤ ይህ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከኢትዮጵያ ባለፈ እጅግ ከፍተኛ አህጉራዊ ፋይዳ አለው።
የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚያደርገው ጥረት ዋና ዓላማው በአፍሪካውያን-መር መፍትሔዎች፣ በጋራ ልምዶች እና በአባል አገራት መካከል መልካም ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ዴሞክራሲን ይበልጥ ማጠናከር እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የእኛ ነባራዊ ሁኔታዎች ልዩ ናቸው። ከሌላው የዓለም ክፍል በቀጥታ ገልብጠን መተግበር የለብንም። ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች የመስጠት አካል በመሆን፣ እኛው ራሳችን መልካም ተሞክሮዎችን በመቅረጽ በመላው አፍሪካ ማስፋትና መጠቀም እንችላለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአህጉራዊው ድርጅት የአፍሪካ ኅብረት መገኛ ናት። በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው አህጉር ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያን ጥበባዊና አርቆ አስተዋይነት የተሞላበት የምርጫ ውሳኔ፣ ሀገሪቱን ወደ ላቀ ጥንካሬና ከፍታ እንደሚያሸጋግርም አመልክተዋል።
የታዛቢ ቡድኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የህግ ማዕቀፍ፣ የምርጫ ሂደቱን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን ተዓማኒ፣ ግልጽ እና ሰላማዊ ምርጫ መርሆዎች ላይ ያተኮረ የማስተዋወቂያ እና የማብራሪያ መድረኮችን እያካሄደ ይገኛል።
የታዛቢ ቡድኑ ከ37 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 73 ታዛቢዎችን ያሰማራ ሲሆን፣ ከቡድኑ አባላት መካከል 61 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ታዛቢዎቹ የምርጫ አስፈፃሚዎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የሥርዓተ-ፆታ ባለሙያዎችን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና የወጣቶች ተወካዮችን አካቷል።
ታዛቢዎቹ በምርጫው ዕለት የሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራትን ማለትም የምርጫ ጣቢያዎች መከፈትን፣ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን፣ የድምፅ ቆጠራውን እና የውጤት ድምር መመዝገቢያ ሁኔታዎችን ለመታዘብና ለመቆጣጠር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ይሰማራሉ።
የአፍሪካ ህብረት ያሰማራው ይህ ቡድን ከ37 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ታዛቢዎችን ማካተቱ ለአፍሪካውያን-መር የምርጫ ታዛቢነት ያለውን ጠንካራ አህጉራዊ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
በተያያዘም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የምርጫ ልዑክ የ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
የኢጋድ ተሳትፎ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ (የአፍሪካ ቀንድ) ያለውን ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ መረጋጋት እና የምርጫ ታዓማኒነት በጋራ ለማጠናከር ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።
ምርጫው በአህጉሪቱ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የአፍሪካውያን-መር የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች እያደገ የመጣውን ሚና የሚያሳይ ትልቅ አጋጣሚ ነው።