AMN – የካቲት 9/ 2018
በኢትዮጵያ እና ቱርክዬ መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን የሚጀምር ጥልቅ ማህበራዊ እና ባህላዊ መሰረት ያለው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ግዙፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊዋ ቱርክዬ ፕሬዘዳንት ጉብኝት ፣ ሐገራቱ ወደ ፊት ትብብራቸውን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የቱርክዬ አምባሳደር በድረገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ እንደ ቱርክዬ የትብብር እና አስተባባሪ ኤጀንሲ (TIKA) እና የቱርክዬ መዓሪፍ ፋውንዴሽን ያሉ ተቋማት በሀገሪቱ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያና ቱርክዬ ፣ በወታደራዊ እና ደህንነት ፣ በልማት እና በባህል ልውውጥ ፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የጠነከረ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የካቲት 2023 እ.ኤ.አ በቱርክዬ ደርሶ በነበረው አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ያሳየችው አጋርነት ያላቸውን ትብብር የሚያመላክት ነው፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሜክሲኮ 100 ቶን የሚመዝን የሰብአዊ እርዳታ ወደ ቱርክዬ በማጓጓዝ እና የኢትዮጵያ የነፍስ አድን ቡድን በቦታው ተገኝቶ በሰጠው አገልግሎት የቱርክዬ መንግስት ከፍተኛ እውቅና እና ሜዳይ መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡
የቱርክዬ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ጉብኝት እ.አ.አ ከ2016 በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ሁለተኛው ጉብኝት ሲሆን፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በታደሰ ሽፈራዉ