AMN- የካቲት 9/2018 ዓ.ም.
የብልጽግና ፓርቲ የ7ኛው አገራዊና ከተማ አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶን እና የምርጫ ምልክት የሆነውን “የስንዴ ነዶ” በአዲስ አበባ ደረጃ ይፋ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ምርጫ ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊና የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚገለጽበትና ሕዝብ በድምጹ መንግሥት የሚመሠርትበትም ሒደት መሆኑን አስታውቀዋል።
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሕዝባችን የገባነውን ቃል፣ ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ በብቃትና በውጤት ፈጽመናል በማለት ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት።
በ7ኛው ዙርም ለሕዝቡ ቃል የምንገባው፣ ከተመረጥን ያለምነውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሌት ተቀን በመሥራት ያለምንም መሸራረፍ እንደምንፈጽም ነው በማለት አብራርተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ማኒፌስቶ ትናንትን ማከሚያ፣ ዛሬን በአግባቡ መጠቀሚያ፣ ነገን መተለሚያና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት አገር ማሻገሪያ መመሪያችን ነው።
የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን የሆነው የስንዴ ነዶም የመደመር፣ የአንድነት፣ የተባብሮ መሥራት፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣ የልዕልና እና የሉዓላዊነት መገለጫ ነው። ይህም በሁላችን፣ ከሁላችን፣ ለሁላችን ብልፅግናን የምናረጋግጥበት ምልክታችን ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ እንደገለጹት፣ ብልፅግና ቃሉን ይጠብቃል፤ ቃሉን ይፈጽማል፤ ሕዝቡን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ያደርጋልም።
ብልፅግናን ይምረጡ ኢትዮዽያን ወደ ተምሳሌት አገር እናሻግር የሚል መልዕክታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስተላልፈዋል።