የቱርክዬ ፊልሞች ከኢትዮጰያ እሴቶች ጋር ምን ያመሳስላል?

You are currently viewing የቱርክዬ ፊልሞች ከኢትዮጰያ እሴቶች ጋር ምን ያመሳስላል?

AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም

የቱርክዬ ፊልሞችና ተከታታይ ድራማዎች በአሁኑ ወቅት ከአሜሪካው ሆሊውድ በመቀጠል በአለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የመታየት ዕድል ያላቸው የጥበብ ውጤቶች ናቸው። የቱርክዬ ድራማዎች ተጽዕኖ ከቢዝነስ አልፎ እስከ ፖለቲካና ባህል ድረስ ይዘልቃል።

ቱርክዬ በፊልሞቿ አማካኝነት የሀገሯን ገጽታ በአለም ላይ ቀይራለች። ብዙ ሰዎች በፊልሞቹ ላይ የሚያዩዋቸውን ታሪካዊ ቦታዎች (እንደ ኢስታንቡልና ካፓዶኪያ) ለመጎብኘት ወደ ቱርክ ይጎርፋሉ። ይህ ለሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የቱሪዝም ገቢ ያስገኛል።

በቋንቋ ረገድም በላቲን አሜሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በባልካን ሀገራት የቱርክን ቋንቋ ለመማር የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የቱርክዬ ፊልሞች እና ድራማዎች ከአገራቸው ወጥተው ከ150 በላይ ሀገራት በመታየት የአለም አቀፍ ገበያ የበላይነት እያገኙ ይገኛሉ።

በተልይም በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ በእነዚህ አካባቢዎች የቱርክ ፊልሞች የሰዎች የዕለት ተዕለት የኑሮ አካል እስከመሆን ደርሰዋል።

በማህበራዊ እሴቶች ለውጥ

የቱርክ ፊልሞች በብዙ ወግ አጥባቂ ማህበረሰቦች ውስጥ አዳዲስ ውይይቶችን ከፍተዋል፡፡ ከሴቶች ሚና አንጻር፤ ጠንካራና ተሟጋች የሴት ገጸ-ባህሪያትን በማሳየት ረገድ ለውጥ እያመጡ እንደሆነ ይነገራል።

ፊልሞቻቸው ዘመናዊ የከተማ ኑሮን ከባህላዊ እሴቶች ጋር አቀናጅተው ስለሚያቀርቡ፣ ” ዘመናዊነትን እንዴት ከባህል ጋር አስተሳስሮ ኑ መጠበቅ እንደሚቻል ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ይመስላሉ።

የቱርክዬ ፊልሞች (Dizis) በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የውጭ ሀገር ፊልሞች ሁሉ በላቀ ሁኔታ ተወዳጅ የሆኑት ዝም ብሎ ሳይሆን፣ በሁለቱ ሀገራት ማህበራዊ እሴቶች መካከል ባለው ጥልቅ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ተመሳሳይነት ነው።

የቤተሰብ መዋቅር እና ክብር

በሁለቱም ባህሎች ውስጥ ቤተሰብ የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ልክ እንደ ኢትዮጵያ፣ በቱርክዬ ፊልሞችም ትልልቅ ቤተሰቦች በአንድ ግቢ ወይም በአንድ ቤት ሲኖሩ ይታያል። ይህ የጋራ ኑሮ ሁለቱን ሀገራት ያመሳስላል፡፡

ለወላጆችና ለታላላቆች የሚሰጠው ልዩ ክብር፣ ምርቃት መፈለግ እና ታላላቅ ሰዎች ሳይፈቅዱ ወሳኝ እርምጃ አለመውሰድ በሁለቱም ዘንድ ተመሳሳይ ነው። የሽማግሌዎች ቃል በሁለቱም ሀገራት ተመሳሳይ አክብሮት አለው፡፡

ማህበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች (Values)

የቱርክዬ ፊልሞች ከሆሊውድ ወይም ከሌሎች የምዕራባውያን ፊልሞች ይልቅ ለኢትዮጵያ ማህበረሰብ ቅርብ ናቸው። በፊልሞቹ የሚታየው የፍቅር መግለጫ፣ አለባበስና ንግግር የኢትዮጵያን የጨዋነት ባህል ብዙም አይጋፉም። እንዲሁም በፊልሞቹ ውስጥ የሚታዩት የጎረቤት መረዳዳት፣ እንግዳን ማክበር እና በችግር ጊዜ ደራሽ መሆን ከኢትዮጵያውያን አብሮነት ጋር በእጅጉ ይጣጣማሉ።

የፍቅር እና የድራማ አቀራረብ

በቱርክዬ ፊልሞች ውስጥ ፍቅር የሚገለጸው በዝግታና በጥልቅ ስሜት ነው። በኢትዮጵያ እንደሚታየው ሁሉ፣ በቱርክ ፊልሞችም የፍቅር ታሪኮች ውስጥ የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት፣ የሀብታምና የደሃ ልዩነት፣ እንዲሁም ለፍቅር የሚከፈል መስዋዕትነት ትልቅ ቦታ አላቸው።

ተመልካቹን የሚያስለቅሱና ልብ የሚነኩ ትዕይንቶች ስሜት በመኮርኮር ረገድ በሁለቱም ባህሎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው።

የከተማና የገጠር ትስስር

እንደ አዲስ አበባ ሁሉ፣ በቱርክ ፊልሞች የሚታዩት የኢስታንቡል ሰፈሮች የድሮና የዘመናዊነት ድብልቅ ናቸው። ሰፈርተኛው የሚተዋወቅባቸው፣ ሻይ/ቡና እየጠጡ የሚያወሩባቸው እና ጎረቤት ለጎረቤት የሚጠባበቅባቸው ትዕይንቶች ለኢትዮጵያ ተመልካች የራሱን ሰፈር ያስታውሱታል።

የምግብና የግብዣ ባህል

በፊልሞቹ ላይ የሚታዩት ትልልቅ የማዕድ ገበታዎች፣ የቡናና የሻይ ስነ-ስርዓቶች እና አብሮ የመብላት ባህል ከኢትዮጵያዊው ማዕድ ማክበር ጋር በእጅጉ ይመሳሰላሉ።

የቱርክዬ ፊልሞች ለምን ተወዳጅ ሆኑ?

የቱርክ ፊልሞች ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ፤የእኛው ታሪክ በሌላ ቋንቋ ተደርገው ይወሰዳሉ። የሆሊውድ ፊልሞች ከእኛ ባህል በጣም የራቁ ሲሆኑ፣ የቱርክ ፊልሞች ግን የራሳችንን የኑሮ ትግል፣ የቤተሰብ ፍቅርና ማህበራዊ እሴቶች ያንጸባርቃሉ።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጽዕኖ የፈጠሩት ዋና ዋና የቱርክ ድራማዎች ውስጥ ጥቁር ፍቅር (Kara Sevda)፤ የጠፋው ስም (Feriha / Adını Feriha Koydum)፤ ኩዚ ጉኒ (Kuzey Güney) እና የመሳሰሉት ፊልሞች በአበዛኛው ኢትዮጰያዊያን ልብ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review