AMN- የካቲት 12/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ እያስመዘገበች ካለዉ ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ የወንጀል መከላከል እና ጸጥታ ስራዎችን ይበልጥ ለማዘመን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግና የተዛቡ መረጃዎችን ማጥራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የትስስር ሰነድ ተፈራርመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገዉ ስምምነት በመዲናዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የወንጀል ቅድመ መከላከል ስራዎችን ለማቀላጠፍ እና የህብረተሰቡን የተባባሪነት ግንዛቤ ለመጨመር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ስምምነቱ የሕዝብን ተሳትፎ ከማሳደግ እና በከተማዋ ሠላምና ፀጥታ ስራዎች ላይ መረጃዎችን ከማጥራት ረገድ አይተኬ ሚና ይኖረዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከተማ ከእለት ወደ እለት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላት ተቀባይነት እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህ የሆነውም ስኬታማ የልማት ተግባራት ከመከናወናቸው እኩል አስተማማኝ ሰላም ማስፈን በመቻሉ እንደሆነ አብራርተዋል።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የማህበረሰቡ ልሳን በመሆን ሃያ አራት ሰባት በአምስት የሀገር ውስጥ እና በሁለት የዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለአድማጭ ተመልካች እንዲሁም አንባብያን ዘንድ እያደረሰ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስፈፃሚዉ ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር መፈራረሙ ሚዲያው በተለያዩ ፕሮግራሞች በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በኩል የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
በታምሩ ደምሴ