AMN- የካቲት 14/2018 ዓ.ም
በትግራይ ክልል ያለው ህጋዊ ያልሆነ ቡድን የባዕዳን ተልዕኮ በመቀበል የትግራይን ህዝብ መከራ እያራዘመ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ::
በአዲስ አበባ ከተለያዩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል::
በውይይት መድረኩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ነዋሪ የትግራይ ተወላጆች ተገኝተዋል::
የትግራይ ለውጥ ፈላጊዎች ንቅናቄ “ሰላም ለህዝባችን፣ ለውጥ ለወደፊት ተስፋችን” በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ክልል የመጣውን ሰላም ወደ ኋላ ለመመለስ ከባዕዳን ሃገራት ጋር ጭምር የሚሰሩ ቡድኖችን በፅናት መታገል እንደሚገባ በመድረኩ ተገልፆል::
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ለውጥን የሚፈልጉ አካላት በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ችግር ለመፋታት መወያየት አስፈላጊ መሆኑ ገልፀዋል::
የትግራይ ህዝብ የባሩድ ሽታ ከአእምሮው ሳይጠፋና እሱን ተከትሎ ከመጣበት ሁለንተናዊ ጉዳት ሳያገግም አሁንም ከጦርነት ውጪ እስትንፋስ በሌላቸውና የራሳቸውን የስልጣን ጥም ለማርካት በትውልድ ህይወት ላይ በሚቆምሩ ቡድኖችን ፈተና ውስጥ ገብቷል ያሉት ሚኒስትሩ ይሄንን ሃገር የማፍረስ ተግባር ባለመቀበል ራሱን ከከንቱ መስዋዕትነት ሊቆጥብ እንደሚገባ ገልፀዋል::
በዳዊት ከበደ