አድዋ፣ በሴቶች ጽናትና ብልሃት የታተመ የነፃነት አሻራ

You are currently viewing አድዋ፣ በሴቶች ጽናትና ብልሃት የታተመ የነፃነት አሻራ

AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም

የአድዋ ተራሮች የታሪክን ጉዞ የቀየረ ታላቅ ድል ሲያስተጋቡ፣ በድምፁ ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች የጀግንነት ቃጭል በጉልህ ይሰማል። አድዋ የወንዶች ጀግንነት ብቻ ሳይሆን፣ የሴቶች የውጊያ ተሳትፎ፣ የስትራቴጂ ጥበብ፣ የስነ-ልቦና የበላይነት እና የጽናት ተምሳሌት ነው።

እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እናቶች በሰሩት ስራ እና በተገኘው አኩሪ ድል ሴቶች የነበራቸው ገድል በታሪክ ፃፊያን ተከትቦ እንደተቀመጠ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

ሴቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት የጦር አመራርና ስትራቴጂ ነዳፊ እንደነበሩ እነዚህ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ማሳያው እቴጌ ጣይቱ የንጉሡ ባለቤት ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸውን ችለው የ6 ሺህ እግረኛና የ6 መቶ ፈረሰኛ ጦር መሪ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

በተለይም የመቀሌውን ምሽግ የውሃ መስመር በመዝጋት ጠላትን ያንበረከከውን ብልህ ስልት የቀየሱት እሳቸው ነበሩ።

ይህንን በተመለከተም አውሮፓዊው የታሪክ ጸሐፊ ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ዘመቻ( The Campaign of Adowa) በተሰኘው መጽሐፉ፣ የእቴጌ ጣይቱን ወታደራዊ ብልሃት ሲገልጽ፤ የመቀሌውን ምሽግ የውሃ መስመር ለማስቆረጥ የሄዱበት መንገድ በጣም ብልህና ለጣሊያን ጦር መፈራረስ ቁልፍ ስልት ነበረ ሲል መስክሯል።

ሌላው በአድዋ ጦርነት ወቅት ሴቶች ከፍተኛ የሞራል ግንባታ እና የስነ-ልቦና ጦርነት ስራ ሰርተዋል፡፡ ሰራዊቱ ወኔው እንዳይላላ በግጥምና በቁጭት በማነቃቃት ረገድ ሴቶች የማይተካ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል፡፡

ይህንን በተመለከተም ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ተክለፃድቅ መኩሪያ በድርሳናቸው እንደገለጹት፣ ሴቶች ከጦር ሜዳው በቅርብ ርቀት ሆነው ወታደሩ ሲሸሽ “ወዴት ትሄዳለህ? እኛ ሴቶቹ እንዋጋለን አንተ እዚህ እደር!” በማለት በቁጭት ያነሳሱ እንደነበር ጠቅሰዋል።

ይህም ወታደሩ ወደ ኋላ ከማፈግፈግ ይልቅ ለሀገሩ እንዲሰዋ ትልቅ ስነ-ልቦናዊ ግፊት አድርጓል።

ሌላው ሴቶች በጦርነቱ ወቅት የስንቅና ሎጅስቲክስ ዋስትና እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ ለ6 ወራት የዘለቀው ጉዞ ሳይስተጓጎል በሺዎች ለሚቆጠር ሰራዊት ስንቅ በማዘጋጀት የጦሩን ህልውና እንዳሰቀጠሉም የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ በታዋቂው “አድዋ” መጽሐፋቸው፣ ሴቶች በጦርነቱ እለት ጥይት በማመላለስ፣ ውሃ በማቀበልና ቁስለኛን በመሸከም የነበራቸው ተሳትፎ ወታደሩ ያለ ስጋት እንዲዋጋ እንዳደረገው በዝርዝር አስፍረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሴቶች ቁስለኞችን በመንከባከብና ለጠላት እስረኞች ጭምር ርህራሄን በማሳየት የሰብአዊነትን ጥግ አሳይተዋል።

በአጠቃላይ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ብቻ ሳይሆን የሴቶች እኩልነትና ጀግንነት የተመሰከረበት የድል አደባባይ ነው።

ዛሬም ታሪክን ስንዘክር፣ የኢትዮጵያን ህልውና በማስቀጠል ረገድ ሴቶች የጽናት እና የድል ዋስትና መሆናቸውን በአድዋ ተምረናል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review