AMN – የካቲት 20/2018 ዓ.ም
ሰላምን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ህዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ወሳኝ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጀነውን 8ኛውን አገር አቀፍ የሰላምና ጸጥታ የጋራ ምክክር መድረክ፣ የሰላም ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ በይፋ አስጀምረናል ብለዋል::
“ሰላማዊ ፖለቲካ ለአገራዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ መድረክ ላይ፤ የሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች፣ የፌደራል ተቋማት እና ሌሎች የሰላምና ጸጥታ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ሰላምን አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ህዝብን የሰላም ባለቤት ማድረግ ወሳኝ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በዚህ ረገድ መዲናችን አዲስ አበባ ስኬታማ ተሞክሮ ያላት በመሆኑ፣ ለሌሎችም ሰፊ ልምድ ታካፍላለች ብለዋል።

የዘላቂ ሰላም መስፈን ለልማት ስራዎቻችን ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፤ የሁሉን አቀፍ ልማት መረጋገጥ ደግሞ በምላሹ አስተማማኝ ሰላምን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በዋናነትም አገራችን ውስጥ ለዘመናት የግጭት ምክንያት የሆኑ ልዩነቶችን በማጥበብ እንዲሁም በብሔራዊ ምክክር በመፍታት፣ የግጭት መንስኤዎችን ከምንጫቸው በማድረቅ እና የህዝብን የሰላም እሴቶች በማዳበር፤ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ለአስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም በጋራ ልንሰራ ይገባል እላለሁ።
ከንቲባ አዳነች አክለውም ሁሉም አካላት ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊነት በቅንጅት ሊሰሩና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ህዝባዊ እና ህጋዊ መንግስት የሚጸናው፣ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ የሆነው ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ተአማኒና አሳታፊ ሆኖ ሲጠናቀቅ በመሆኑ፤ ሁላችንም ለዚህ ስኬት ኃላፊነታችንን እንወጣ።
ክቡራን የመድረኩ ተሳታፊዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የዲፕሎማሲ፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት ከተማ በሆነችው መዲናችሁ አዲስ አበባ የሚኖራችሁ ቆይታ እጅግ ፍሬያማ እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።