የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት

You are currently viewing የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት

በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁርና ጭቁን ሕዝቦችን ታሪክ በመቀየር ረገድ የዓድዋ ድል ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ተጠቁሟል

ደስታ መብራቱ (ፕ/ር) በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጣና ምክትል ዳይሬክተር መሆንን ጨምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። በተለያዩ አጋጣሚዎችም በርካታ አገራትን የመጎብኘትና የማየት ዕድልም አጋጥሟቸዋል።

 አግራሞትና ሐዘኔታ ከፈጠረባቸው የጉብኝት አጋጣሚዎች መካከል በሴኔጋል ጎር ደሴት ያደረጉት ይጠቀሳል። የጎር ደሴት በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ዘመን (ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን) አፍሪካውያን በባርነት ወደ አሜሪካና ካሪቢያን ደሴቶች እስኪሄዱ ድረስ በእስር የሚቆዩበት የማሰቃያ ስፍራ ነው። ደስታ (ፕ/ር) አብረዋቸው ሲጎበኙ ከነበሩት አብዛኞቹ ከሰሜን አሜሪካ የመጡና አያቶቻቸው ከምዕራብ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ታፍነው በባርነት የተሸጡ መሆናቸውን የሚያውቁ ናቸው። ስለሆነም የቀደምት አያቶቻቸውን የመከራና ስቃይ ጉዞ ተሸክመው በከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ይጎበኙ እንደነበር “የትውልድ ውርስ፤ ከመተሐራ እስከ ፓሪስ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል።

“የባሕሩን ጉዞ ተቋቁመው ጥሩ ዋጋ ሊያወጡላቸው የማይችሉትን አፍሪካውያን የሚያስወግዱበት መንገድ፣ እጅና እግራቸው ታስሮ ወደ አሜሪካ እስከሚጓዙ ድረስ የሚቆዩበት ምድር ቤት ውስጥ ምግብ የሚመገቡበትና የሚጸዳዱበት ሁኔታ እና በመጨረሻም ወደ አሜሪካ የሚወስዳቸው መርከብ ላይ የሚሳፈሩበትን ቀጭን የሲኦል ቦይ ሲመለከቱ የሚሰማዎት የመንፈስ ስብራት እና ቁጣ በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል” ይላሉ ደስታ (ፕ/ር)።

በዚህ እንደ ሰው ልጅና አፍሪካዊነት ጥቅል ሐዘን እንደተሰማቸው የሚገልጹት ደስታ (ፕ/ር)፣ መንፈሳቸው ጠንካራ እንዲሆንና እንዲጸናኑ የሚያደርጋቸው አያት ቅድመ አያቶቻቸው ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅና ለመከላከል የከፈሉት መስዋዕትነት በማስታወስ እንደሆነ አክለው አስፍረዋል።

አዎ! ኢትዮጵያውያን የአገርን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የከፈሉት መስዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አይደለም። በየዘመናቱ በከፈሉት መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ ዘልቋል። ኢትዮጵያ ከራሷ ባሻገር አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር እንዲላቀቁ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁርና ጭቁን ሕዝቦች ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉና መብታቸውን ለማስከበር እንዲነሳሱ ተምሳሌት መሆን ችላለች። የኢትዮጵያን፣ የአፍሪካን፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁርና ጭቁን ሕዝቦችን ታሪክ በመቀየር ረገድ የዓድዋ ድል ትልቁን ሚና ተጫውቷል።

የታሪክ ተመራማሪው ኤርሚያስ ጉልላት (ዶ/ር) “የዓድዋ ጦርነት እና የዓለም ቅኝ ግዛት አሰላለፍ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ አፍሪካውያን በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ዘመን (ከ16ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን) ለ300 ዓመታት ሰብአዊ ክብራቸው ተዋርዶ እንደ እንስሳ ተቆጥረው፤ እንዳይጠፉ በሰንሰለት ታስረው ይሸጡ ነበር። አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች “ነጮች የተለዩ ሕዝቦች ናቸው፤ የሰው ልጆች በአፈጣጠራቸው የተለያዩ ናቸው፤ ነጮች ከጥቁሮች የተለዩ ምርጥ ዘሮች ናቸው” የሚለውን የእንግሊዛዊ ሳይንቲስት ቻርለስ ዳርዊንን የፍጥረታት አመጣጥ (The Origin of Species) እሳቤ በመከተል ብዝበዛና ቅኝ ግዛቱን ተገቢ እንደሆነ አድርገው ይወስዱት ነበር።

አየለ በከሪ (ፕ/ር) የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። ለአሥራ አራት ዓመታት ያህል በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአፍሪካ ታሪክ፣ ሥልጣኔና ባሕል ዙሪያ እንዲሁም መቀሌ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክ አስተምረዋል። እሳቸው እንደሚናገሩት፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ1885 አውሮፓውያን በበርሊን በመሰባሰብ አፍሪካን እንደ ቅርጫ በመከፋፈል በርካታ የአፍሪካ አገራት በቅኝ ግዛት ሥር አደረጉ። ኢትዮጵያንም ጣሊያን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል ስትነሳ በቀላሉ እንደምታሸንፍ በቅኝ ገዥ አውሮፓውያን ዘንድ ታምኖ ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በሚገባ በመደራጀት፣ ‘አገር የሞተ እንደሆነ ወዴት ይደረሳል’ በሚል እሳቤ በተባበረ ኃይል በመፋለም አሸነፉ።

ኢትዮጵያ በማይቀለበስ መልኩ ጣሊያንን ያሸነፈችበት የዓድዋ ጦርነት የራሷ ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ከማስቻል ባለፈ በአፍሪካና በመላው ዓለም በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገራት የፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎ እንዲፋፋምና ነፃነታቸውን እንዲያገኙ በር ከፈተ። ‘ኢትዮጵያውያን ቅኝ ሊገዛቸው የመጣውን ጠላት አሸንፈዋል፤ እኛም ቅኝ ገዥዎችን በመታገል ድል ማድረግ እንችላለን’ በማለት እንዲነሳሱ ምክንያት እንደሆነ አየለ (ፕ/ር) ያስረዳሉ።

የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) እንደሚገልጹት፣ ዓድዋ አፍሪካውያንና መላው ጥቁሮች ከሰው በታች እንደ እንስሳ፣ ተሸናፊ፣ ደካማ፣ የማያስቡ ተደርገው የሚታዩበትን የተዛባ አመለካከት ቀይሯል። በአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ዘመን ጥቁሮች እንደ ሰው አይቆጠሩም ነበር፤ ከእንስሳትና ዕቃ እኩል ተቆጥረው በባርነት ይሸጡ ነበር። በቅኝ ግዛት ዘመንም ሀብታቸውን ከመበዝበዝ ባሻገር በሐሰት ትርክት ዝቅ ተደርገው ይታዩ ነበር፤ ለተመሳሳይ ሥራ አነስተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው፣ ረጅም ሰዓት እንዲሠሩ እየተደረገ መብታቸው ተገፍፎ በተለያየ መልኩ ይጨቆኑ ነበር። የዓድዋ ድል በአፍሪካውያንና ጥቁር ዘሮች ላይ ይራመዱ የነበሩ የተዛቡ አስተሳሰቦች እንዲቃኑ አድርጓል። አፍሪካውያን ከነጮች ጋር እኩል እንደሆኑ፣ ማሰብ፣ መሥራት፣ ማሸነፍ እንደሚችሉና አላግባብ ይሰጣቸው የነበረ አተያይ እንዲቀየርና ተገቢ ያልሆኑ የመብት መነፈጎች እንዲቀሩ ምክንያት ሆኗል።

የታሪክ ተመራማሪው ኤርምያስም (ዶ/ር)፣ በመጽሐፋቸው “የዓድዋ ጦርነት በአካል በሥጋ በገሃድ ፍልሚያው የተካሄደው በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ነበር። የዓድዋ ጦርነት በመንፈስ የተካሄደው በዓለም ጥቁር ሕዝቦችና በአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ኃይሎች መካከል ነበር” ሲሉ አስቀምጠዋል። አክለውም በዓድዋ ጦርነት የተገኘው ድል የአፍሪካ ድል ነው። የአውሮፓ ቅኝ ግዛት መመሪያ የበርሊን ጉባኤ እንዲፈረካከስ ያደረገ ድል ነው። የሰው ልጅ እኩልነት የታየበት ሲሆን አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ እንዲታገሉ ያነሳሳ ከፍተኛ የታሪክ ምዕራፍ ነበር።

 የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የአፍሮ አሜሪካውያን ካሪቢያን ድል ነው። ከአፍሪካ ቅኝ ግዛት እንዲወገድና ነጭ መሸነፍ እንደሚችል አስተምሯል። የአውሮፓ ቅኝ አገዛዝ ከመላው አፍሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ እስያ፣ ካሪቢያን ደሴት እንዲወገድ ያደረገና ጥቁር ሕዝቦችን የቀሰቀሰ እንደሆነም አስፍረዋል።

የታሪክ ተመራማሪው አየለ (ፕ/ር) እንዳብራሩት፣ በቅኝ ግዛት ዘመን እንደ አልጀሪያ፣ ማሊ፣ ኬንያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያና ሌሎችም የአፍሪካ አገራት ቅኝ ግዛትን ለማስወገድ ትግል ሲያደርጉ ነበር። የዓድዋን ጦርነት ልዩ የሚያደርገው የተገኘው ድል ውጤቱ የማይቀለበስ ስለነበር፣ አፍሪካውያንና በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝቦች ተስፋ ባለመቁረጥ ለነፃነትና እኩልነት ትግላቸውን እንዲያፋፍሙ ተምሳሌት መሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያን ‘እኛ ባሪያ የምንሆን ሕዝቦች አይደለንም፤ ሁለተኛ ዜጋ፣ የቅኝ ገዥዎች አገልጋይ አይደለንም’ ብለው በመነሳት፣ ስልትና ስትራቴጂ በመቀየስ፣ ጠላትን ሲደመስሱ፣ የደመሰሱት ኢ-ፍትሐዊነትን፣ አድሎአዊነትን፣ አንዱ የበላይ ሌላውን የበታች የሚያደርገውን አመለካከት ነው። በዚህ ደረጃ ሲታይም ዓድዋ ጥልቅ የሆነ ፍልስፍና ነው።

አሜሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ ራይሞንድ ጆናስ (ፕሮፌሰር) “የዓድዋ ድል” በተሰኘው መጽሐፋቸው በዓድዋ ጦርነት ጣሊያን በዘመናዊ እና እስከ አፍንጫዋ በታጠቀ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር ብትሞክርም፤ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ወኔና መስዋዕትነት ጦርነቱን አሸንፈዋል። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫ የቀየረ ነው ብለዋል።

“በታሪክ ጥቁር ሕዝቦች ነጭ ወራሪን እስከመጨረሻው ድል ያደረጉበት የመጀመሪያው ክስተት ነበር። አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ አሜሪካውያንን ጨምሮ ሌሎች የቅኝ ግዛት ሰለባ አገራት በዓድዋ ድል በተፈጠረ መነሳሳት ምክንያት ፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ጀምረዋል። ከድሉ በኋላ ቅኝ ገዥዎችም የግዛት ማስፋፋታቸውን ገትተዋል” በማለት ነው የገለጹት።

በጥቅሉ ዓድዋ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከተመዘገቡና የዓለምን አካሄድ ከቀየሩ ክስተቶች መካከል አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። ዓለም አፍሪካውያንን፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁርና ጭቁን ሕዝቦችን ይመለከትበት የነበረውን የተዛባ አተያይ የቀየረ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ። ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል የተነሳ በአፍሪካውያንና በመላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድም የላቀ ቦታ እንዲሰጣት አድርጓል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ፣ የተለያዩ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መሰባሰቢያ እንድትሆን በማድረግ ረገድ ድሉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review