AMN የካቲት 22/2018
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኮማንደር አትሌት ጌጤነሽ ኡርጌን ጨምሮ በተለያዩ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ አትሌቶች ድጋፍ አድርገዋል፡፡
አትሌት ኮማንደር ጌጤነሽ ኡርጌ ባጋጠማት የጤና መታወክ ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጣ ልጆቿን ለማስተማር ከመቸገር ጀምሮ ወደ ገጠር ገብቶ ከዘመድ እስከ መጠጋት ያደረሰ ችግር ገጥሟት ነበር፡፡
የዚህች የሀገር ባለውለታ ያለችበትን ሁኔታ የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አትሌቷን ጨምሮ ለሌሎች የሀገር ባለውለታ አትሌቶች ወገናዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አትሌቶቹ የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን እና ሀገርም ውለታቸውን የማትረሳ መሆኑን ገልጸው እነዚህ ብሄራዊ ጀግኖች በችግር ወድቀው መመልከት ልብን የሚነካ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አትሌቶቹ የወጣትነት ዘመናቸውን ሁሉ ለሀገራቸው መስጠታቸውን የሚናገሩት ከንቲባ አዳነች አትሌቶቹ በችግር ውስጥ ሲወድቁ ሀገራቸው እንደማትዘነጋቸው ገልጸዋል፡፡
ከኮማንደር አትሌት ጌጤነሽ በርቄ ጋር በተያያዘ ከተማ አስተዳደሩ የህክምና ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ከጎኗ በመሆን ይከውናል ብለዋል፡፡
ድጋፉን በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የማስተባበር ኃላፊነት ሲወጣ እንደነበር የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
የቀድሞ አትሌቶቹ ስለተደረገላቸው ድጋፍ ከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ በሂደቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ችግር ውስጥ የሚገኙ የሀገር ባለውለታ ዜጎችን የመደገፍ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል፡፡
ዛሬ በተከናወነው ድጋፍ ለአትሌት ኮማንደር ጌጤ ኡርጌ 10 ሚሊዮን ብር፣ ባለ 3 መኝታ የመኖሪያ ቤት ከሙሉ የቤት እቃ ጋር እንዲሁም አትሌቷ ካለችበት የጤና ሁኔታ አንፃር በጤና ቀጣይ ህክምና ድጋፍ እንድታገኝ የሚደረግ ሲሆን: አትሌት ዋሚ ቢራቱ፣ አትሌት አጥሬ በዛብህ፣ አትሌት ሸዋንግዛው ወርቁ፣አትሌት ወርቁ በሮ፣ አትሌት ግርማ ወ/ሃና፣ አትሌት ሸምሱ ሀሰን፣ አትሌት ሻይቱ ሽፈራው፣ አትሌት ዘውዴ ሀ/ማሪያም፣አትሌት ጌታቸው ከበደ እና አትሌት ወልዴ ሮባሌ ለእያንዳንዳቸው የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል።
በሃብታሙ ሙለታ